ኢትዮጵያ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ተክላለች?

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ በመላው አገሪቱ በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸው መነገሩ ይታወሳል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ በመላው አገሪቱ በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸው መነገሩ ይታወሳል

ኢትዮጵያ በሦስት ወራት ውስጥ አራት ቢልዮን ዛፎች ለመትከል ማቀዷን ይፋ ያደረገችው አምና ነበር።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ በመላው አገሪቱ በአንድ ቀን 350 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ተወጥኖ በርካቶች መሰማራታቸው ይታወሳል። ነሀሴ መጨረሻ ላይ መንግሥት ግቡን እንደመታም ይፋ አድጓል።

ለመሆኑ በነበረው አጭር ጊዜ የተባለውን ያህል ችግኝ መትከል ይቻላል? የተያዘው እቅድ ግቡን ለመምታቱስ ምን ማስረጃ አለ? የሚለውን የቢቢሲው 'ሪያልቲ ቼክ' ፈትሿል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተቀናበረው የግሪን ሌጋሲ የችግኝ ተከላ ሳምንት አልፎታል።

'አረንጓዴ አሻራ' የተባለው የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ዘመቻ፤ በመላው ዓለም ያሉ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን በችግኝ ዘመቻ ተምሳሌት አድርገው እንዲያነሷት ምክንያት ሆኗል። የተፈጥሮ ኃብት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ግብርና እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቀልበስም እንደ ምሳሌ ተጠቅሳለች።

በቅርቡ በእንግሊዝ ምርጫ ሲካሄድ፤ አውራዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎችን እንደሚተክሉ ቃል ሲገቡ፤ ማጣቀሻ ያደረጉት የኢትዮጵያን ተነሳሽነት ነበር።

'ሌበር ፓርቲ' እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2040 ሁለት ቢሊዮን ዛፎች እንደሚተክል፣ ወግ አጥባቂዎች ደግሞ በየዓመቱ ቢያንስ 30 ሚሊዮን ዛፎች ለመትከል መወጠናቸውን ገልጸዋል። 'ግሪን ፓርቲ' በበኩሉ በ2030 700 ሚሊዮን ዛፎች እንደሚያደርስ ቃል ገብቷል።

ካናዳ በቀጣይ አሥር ዓመታት ሁለት ቢሊዮን ዛፎች የማብቀል እቅድ ነድፋለች።

ክብረ ወሰን የመስበር ውጥን

ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ. ም. ኢትዮጵያ አንድ ቀን የወሰደ የችግኝ ተከላ ዘመቻ አከናውናለች። የታቀደው በመላው አገሪቱ 200 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ነበር። የኋላ ኋላ ግን መንግሥት ከታቀደው በላይ በ12 ሰዓት ውስጥ 353,633,660 ችግኝ መተከሉን ይፋ አደረገ።

የችግኝ ተከላ ዘመቻው ሲተዋወቅ፤ የዓለም ክብረ ወሰንን መስበር እንደ አንድ ግብ ተይዞ ነበር። ሆኖም ቢቢሲ ለ'ጊነስ ወርልድ ሬከርድ' ጥያቄ ሲያቀርብ፤ ገና ማስረጃ እንዳልቀረባቸው ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኢትዮጵያ በሦስት ወራት ውስጥ አራት ቢልዮን ዛፍ ለመትከል መወጠኗን ይፋ ያደረገችው አምና ነበር

የተቋሙ ቃል አቀባይ ጀሲካ ስፒሌን "የመረጃ አጣሪ ክፍላችን እንዲያረጋግጥ፤ አዘጋጆቹ ያላቸውን ማስረጃ እንዲያሳውቁን እንጠይቃለን" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ፤ ተተከለ ስለተባለው የችግኝ ብዛት እንዲሆም መረጃው እየተጣራ ስለመሆኑ እንዲያብራራልን ብንጠይቅም፤ በችግኝ ተከላው ዙርያ ላሉ ብዙ ጥያቄዎች ኢትዮጵያ ምላሽ እንደሰጠች በመግለጽ፤ አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።

አራት ቢሊዮን ዛፎች መትከል ይቻላል?

በሦስት ወራት ውስጥ አራት ቢልዮን ዛፎች ለመትከል ሲወጠን፤ በቀን ቢያንስ 45 ሚሊዮን ዛፎች ይተከላሉ ማለት ነው።

በአንድ ቀን (ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ. ም.) 350 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ከግምት ብናስገባ፤ የዘመቻውን ግብ ለመምታት በተቀመጠው የጊዜ ክልል ውስጥ በቀን 40 ሚሊዮን ችግኝ መትከል ያስፈልጋል።

የመንግሥት እቅድ ዛፎቹን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ፣ በ6.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ መትከል ነው።

የፎቶው ባለመብት, Girmay Gebru, BBC

የምስሉ መግለጫ,

በትግራይ ክልል የተተከሉት አዳዲስ ችግኞች አካባቢው ደረቅ በመሆኑ ሳቢያ ለማደግ እየታገሉ ነው

የአንድ ዛፍ መጠነ ስፋት በአማካይ በሄክታር 1,500 ነው ብንል፤ አራት ቢልዮን ዛፎችን መትከል የሚያስችል በቂ መሬት አለ ማለት ነው። ሆኖም ይህ ስለተተከሉት ችግኞች የሚነግረን ነገር የለም።

ያለን መረጃ የተገኘው ከመንግሥት ሲሆን፤ መረጃው በሦስት ወራት ውስጥ ከ3.5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች እንደተተከሉ ይጠቁማል። በተጨማሪም ያልተተከሉ 1.3 ቢልዮን ችግኞች ፈልተዋል።

ይህ ሁሉ ዛፍ የሚቆጠረው እንዴት ነው?

ሁሉንም ዛፎች መቁጠር ባንችልም፤ በቅርቡ የተተከሉ ችግኞች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች በአንዱ ተገኝቶ ፎቶ እንዲያነሳ ዘጋቢያችንን ልከን ነበር። በትግራይ ክልል የተተከሉት አዳዲስ ችግኞች አካባቢው ደረቅ በመሆኑ ሳቢያ ለማደግ እየታገሉ ነው።

የሳተላይት ፎቶ የሚያጠና ድርጅትም አነጋግረን ነበር። ድርጅቱ አዲስ የተተከሉትና በመጠን አነስተኛ የሆኑትን ችግኞች ከእርሻ መሬት ለመለየት አዳጋች እንደሆነ ገልጾልናል።

በተባበሩት መንግሥታት የደን ባለሙያ የሆኑት ቲም ክሪስቶፈርሰን፤ የዛፍ ተከላው ተግዳሮቶች ላይ ምንም ባይሉም፤ ኢትዮጵያ የደን ሽፋኗን ለማስፋት የምታደርገው ጥረት እንደሚያበረታታቸው ይናገራሉ።

"ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በችግኝ ተከላው በተለይም ደግሞ ዛፎቹን በመንከባከብ ረገድ ድጋፍ እንዲሰጣት ጠይቃለች" የሚሉት ባለሙያው፤ አገሪቱ በ2030፤ 15 ሚሊዮን ሄክታር የሚደርስ የተመነጠረ ደን እንዲያገግም ቃል መግባቷን ይናገራሉ። እንቅስቃሴው የደን ምንጣሮን ለመከላከል የተጀመረ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ አካል ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ዛፍ ተካላ ከግብርና መሬት ፍላጎት ጋር መመጣጠን አለበት

ኢትዮጵያ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎች ለመትከል ማቀዷ፤ በአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ቢመሰገንም፤ በተያዘው ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ችግኝ እንደተተከለ ለመለካት ይሄ ነው የሚባል ሥራ አልተሠራም።

ኢትዮጵያን አረንጓዴያማ ለማድረግ፤ ሐምሌ ላይ የአውሮፓ ኅብርት እና ኢትዮጵያ የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተፈራርመው ነበር።

በመላው አገሪቱ የሚገኙ አገር በቀል ድርጅቶች፤ ችግኞች እንዲተክሉ የገንዘብ ድጋፍ ተሰጥቷቸዋል። ድርጅቶቹ ከተተከለው ችግኝ የበለጠ ቁጥር ለክልል ኃላፊዎች ነግረው፤ ኃላፊዎቹም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚሰበሰበው መረጃ ቁጥሩን መስጠታቸውን ማወቅም ብዙ አያስገርምም።

ለወደፊት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች

የተተከለው ችግኝ ብዛት ምንም ይሁን ምንም፤ ኢትዮጵያ የደን ምንጣሮን ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ አይካድም።

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 40 በመቶ ነበር። አሁን ግን ወደ 15 በመቶ አሽቆልቁሏል።

የችግኝ ተከላ ዘመቻው ይህንን ችግር እንዲቀርፍ ከተፈለገ፤ ችግኞቹን በየጊዜው ውሀ ማጠጣት ያስፈልጋል። በእርግጥ የውሀ እጥረት ባለበት አገር ውስጥ ይህንን እውን ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

በውሀ ጥበቃ ዙርያ የተሻለ አካባቢ ሊፈጥርም ይችላል።