ከአለቃ ጋር አንድ ሁለት ማለት ያዋጣል?

መጠጥ ቤት ውስጥ ብርጭቆ የሚያጋጩ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ28 ዓመቱ ሪኮ ኪታማውራ ከኮሌጅ ከተመረቀ በኋላ የገበያ ጥናት በሚያደርግ ተቋም ውስጥ ነበር የተቀጠረው።

ጃፓናዊው ሪኮ የተቀጠረበት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ከሥራ በኋላ ሰብሰብ ብለው መጠጥ የመቀማመስ ልማድ ነበራቸውና ሪኮም ይቀላቀላቸው ጀመር። ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የጠጣበትን ቀን አይረሳውም።

"ብዙ ለመጠጣት ተገድጄ ነበር፤ ከእነሱ እኩል ለመሆን በፍጥነት ስጠጣ ቶሎ ሰከርኩ"

ጃፓን ውስጥ ከሥራ በኋላ መጠጣት የተለመደ ነው። ከሥራ ባልደረቦች ጋር መጠጣት 'ኖሚኬይ' ይባላል። ማኅበራዊ መስተጋብርን እንደሚያጠናክርም ይታመናል።

ይህ ልማድ ቀጣሪዎች ሥልጣናቸውን ያላግባብ እንዲጠቀሙ መንገድ ከፍቷል ስለተባለ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መጥቷል።

ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም፤ አንዳንድ ተቀጣሪዎችን ከመነጠል አካላዊ ጥቃት እስከማድረስ ይሄዳል።

የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያው ኩሚኮ ንሞቶ እንደሚሉት፤ አንድ ሠራተኛ ከሌላው ጋር አብሮ እንዲጠጣ ማስገደድ እንደ ብዝበዛ ይታያል።

"ቀደም ባለው ዘመን አንድ የሥራ ቦታ ልማድ ነበር፤ አሁን ግን ሥልጣን የመበዝበዣ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል" ሲሉ ያስረዳሉ።

የጃፓን መንግሥት፤ ቀጣሪዎች ሥልጣናቸውን ያላግባብ እንዳይጠቀሙ በሚቀጥለው ዓመት አዲስ ሕግ የመተግበር እቅድ አለው። ጃፓን ለሰዓታት የሚሠሩ፣ በሥራ ጫና ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችም ያሉባት አገር ናት። የአገሪቱ መንግሥት መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ሕጉ እንደሚረዳው ተገልጿል።

አሁን አሁን ቀጣሪዎች፤ ሠራተኞቻቸው አብረዋቸው እንዲጠጡ የመጋበዝ ፍላጎታቸው እየቀነሰ መጥቷል።

ሪኮ ኪታማውራ እንደሚናገረው፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአለቆች ጋር መጠጣት ግዴታ አይደለም ተብሏል።

የ47 ዓመቱ ታትስ ካቱስኪ፤ የአንድ የንግድ ተቋም ኃላፊ ናቸው። ሠራተኞቻቸው በጋራ እንዲጠጡ እንደማያስገድዱ ይናገራሉ።

ባለፉት አምስት ዓመታት የአመለካከት ለውጥ እየመጣ እንደሆነ ያስረዳሉ። እሳቸው የዛሬ ሀያ ዓመት ሥራ ሲጀምሩ ከነበረው የአሁኑ የተለየ እንደሆነም ያክላሉ። ያኔ በሳምንት ቢያንስ ለአራት ቀን ገደማ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ይጠጡ ነበር።

"አለቃህ ና እንጠጣ ሲል 'አምቢ' ማለት አይቻልም።"

እስከ እኩለ ሌሊትና ከዚያም በላይ ይጠጡ ስለነበረ በነጋታው ይታመሙም ነበር። ሆኖም ግን አለቃቸውን የተሻለ የሚያውቁበት አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

ጃፓን ውስጥ ከሥራ ጋር በተያያዘ መጠጥ መቀማመስ እየቀረ መጥቷል። አለቆች 'ሠራተኞቻቸውን እየበዘበዙ ነው' መባል ስለሚያስፈራቸውም፤ ተቀጣሪዎችን መጠጥ መጋበዝ ቀንሰዋል።

በሌላ በኩል አዳዲስ ተቀጣሪዎች ነገሩ እንደተጋነነ ያስባሉ።

ታትስ ካቱስኪ እንደሚሉት፤ አዳዲስ ተቀጣሪዎች 'እንጠጣ' አለመባላቸው ቅያሜ ይፈጥርባቸዋል።

"ተቀጣሪዎቹ እንደተተዉ ይሰማቸዋል። መጠጥ ማኅበራዊ ግንኙነትን ያጠነክራል፤ ከአለቃ ጋር ለመቀራረብም ይረዳል። አንዳንድ ተቀጣሪዎች አለቆቻቸው ለምን አብረን እንጠጣ እንዳላሏቸው ይጠይቃሉ።"

የሶፊያ ዩኒቨርስቲው ፓሪሳ ሀግሂሪያን እንደሚሉት፤ አብሮ በመመገብ እና በመጠጣት ማኅበራዊ መስተጋብርን ማጠናከር ይቻላል።

"ጃፓን ውስጥ ሰዎች መጠጣት ይወዳሉ፤ መጠጥ እና ሲጋራ እንደሚያዝናኑ ይታመናል፤ በጋራ የሚደረጉ ነገሮች አካል መሆን መልካም ነው" ሲሉም ያስረዳሉ።