ኢድሪስ ኤልባ የሴራ ሊዮን ዜግነት ሊሰጠው ነው

ኢድሪስ ኤልባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዝነኛው ተዋናይ ኢድሪስ ኤልባ የወላጅ አባቱ የዘር ሐረግ የሚመዘዝባት ሴራ ሊዮን ዜግነት ሊሰጠው መሆኑ ተነገረ።

እንግሊዛዊው የፊልም ተዋናይ ለጉብኝት ከትናንት በስቲያ ነበር ወደ ሴራ ሊዮን መዲና ፍሪታዎን ያቀናው።

ኤልባ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ሲናገር "ከየትኛውም ሃገር ዜግነትን የማግኘትን ያክል ክብር የለም" ብሏል።

"ለአፍሪካ አዲስ አይደለሁም። ከዚህ በፊት ወደ አፍሪካ መጥቻለሁ። ብዙ ፊልሞችን በአፍሪካ ሰርቻለሁ። ለሴራ ሊዮን ግን የተለየ ስሜት ነው ያለኝ ምክንያቱም የወላጆቼ ሃገር ነውና" ብሏል ኤልባ።

ኤልባ የፈረንጆቹን ገና በሴራሊዮን እንደሚያሳልፍ እና በአንድ ታዋቂ ደሴት ላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቱን ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ኤልባ በሴራ ሊዮን ቆይታው ከሃገሪቱ ፕሬዝደንት እና አድናቂዎቹ ጋር ይገናኛልም ተብሏል።

'አቬንጀርስ' ጨምሮ በበርካታ ማርቭልስ ፊልሞች ላይ የተወነው ኤልባ 'ፒፕል' በተሰኘው መጽሄት የ2018 "የዓለማችን አማላይ ወንድ" ተብሎም ተመርጧል።

ኤልባ የሴራ ሊዮን ፓስፖርት ማግኘቱ በፈቀደው ሰዓት ወደ 'ሃገሩ' እንዲመጣ ያስችለዋል መባሉን የሴራ ሊዮን መገናኛ ብዙሃን የሃገሪቱን ባለስልጣናት ጠቅሰው ዘግበዋል።