ሶማሊያዊያን የአንበጣውን መንጋ ለምግብነት በማዋል እየተዋጉት ነው

አንበጣ ለምግብነት ሲዘጋጅ

የፎቶው ባለመብት, Universal Somalia

በሰሜናዊ የኢትዮጵያ ክፍል እንደተስተዋለው ሁሉ ጎረቤት ሃገር ሶማሊያም በ25 ዓመታት ውስጥ አይታ የማታውቀው ከፍተኛ የአንበጣ መንጋ ወረራ አጋጥሟታል።

በሃገራችን የአንበጣውን መንጋን ከፍተኛ ድምጽ በማውጣት ነበር ህዝቡ ከአካባቢው ሲያባረው የቆየው።

የጎረቤት ሃገር ሶማሊያ ዜጎች ግን መፍትሄ ያሉትን ሌላ መላ ዘይደዋል። ይህም፤ የአንበጣ መንጋውን መያዝ፣ በውሃ መዘፍዘፍ፣ አጠንፍፎ በዘይት ጠብሶ መመገብ።

በሶማሊያ አዳዶ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች አንበጣን ጠብሰው ከሩዝ እና ከፓስታ ጋር ለምግብነት እያዋሉት ነው።

አንዱ የከተማዋ ነዋሪ "አንበጣው ከአሳ በላይ ልዩ ጣዕም አለው" ያለ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የአንበጣው የንጥረ ነገር ይዘት ፍቱን የሆነ መድሃኒት እንደያዘ እንደሚያምን ይናገራል።

ይሄው ግለሰብ ዩኒቨርሳል ሶማሊያ ለተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ አስተያየቱን ሲሰጥ፤ አንበጣው ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር የደም ግፊቱን እንደሚያስተካክልለት እና የጀርባ ህመሙን እንደሚያሽልለት ተስፋ አድርጓል።

ዩኒቨርሳል ሶማሊያ ቴሌቪዥን ነዋሪዎች በምን አይነት መልኩ አንበጣውን አብስለው ለምግብነት እንደሚያቀርቡት አስመልክቷል።

አንበጣው በቅድሚያ ተሰብስቦ ከተያዘ በኋላ በእቃ ውስጥ ተከድኖበት ይቆያል። ከዚያም በውሃ ይዘፈዘፋል። ውሃ ውስጥ ተዘፍዝፎ እንዲቆይ የተደረገው አንበጣ ይጠነፈፋል ከዚያም በዘይት ይጠበሳል።

አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በአካባቢው የሚገኙ ምግብ ቤቶች ከአንበጣ የሚሰሩ ምግቦችን በምግብ ዝርዘሮቻቸው ውስጥ እንዲያካትቱ እየጠየቁ ነው።

በሶማሊያ አንበጣን በምንም አይነት መልኩ የመመገብ ልምድ ከዚህ ቀደም ታይቶ እንደማይታወቅ ተነግሯል።

በምዕራብ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና በኢሲያ የሚገኙ አንዳንድ ሃገራት አንበጣን ለምግብነት የማዋል ባህል አላቸው።