የሐኪሞች እጅ ጽሑፍ የማይነበበው ለምንድን ነው?

የህክምና ወረቀት

የፎቶው ባለመብት, BSIP

በተለያየ ምክንያት የሕክምና ደጃፍ ይረግጣሉ። ቀላል ለሆነ ራስ ምታትም ሆነ ተኝቶ ለመታከም ፈውስ በእጁ ነው የተባለ ዶክተር ባለበት እርስዎ አይጠፉም።

'አይ እኔ ለበሽታ እጅ አልሰጥም' ቢሉ እንኳ አንድ ቀን እግር ጥሎዎት ሐኪም ፊት መቅረብዎ አይቀርም።

ለሐኪሙ 'ሽቅብ ሽቅብ ይለኛል'፤ 'ወገቤን ከፍሎ ያመኛል'፤ 'ጭው እያለ ይዞርብኛል'. . . ካሉት በኋላ ነጭ ወረቀት ላይ እንደ ነገሩ የተሞነጫጨረ ነገር ጽፎ ይሰጥዎታል።

ትዕዛዙ ይለያያል፤ ወይ ወደ መድሃኒት ቤት፤ አልያም ላብራቶሪ ወይንም አልትራሳውንድ፣ ራጅ ብቻ እንደ በሽታዎ አይነት ያስፈልጋል ያለውን ይጽፍልዎታል።

እርስዎም ፊደል የቆጠሩ ስለሆኑ ምን ተጻፈ ብለው አይንዎን ወረቀቱ ላይ ያንከራትታሉ። ምንም ያህል ቢማሩ ግን የዶክተሩን የእጅ ጽህፈት ምስጢር ሊደርሱበት አይቻልዎትም።

የጻፈው በምን ቋንቋ ነው? ሊሉም ይችላሉ።

ኢትዮጵያ ሁሉም ሀኪሞች በእንግሊዘኛ ነው የሚጽፉት።

እርስዎ ግን የእነርሱን እንግሊዘኛ ማንበብም ሆነ መገመት የእንጦጦ ዳገት ነው የሚሆንብዎ። ለምን?

የሐኪሞች እጅ ጽሑፍ ለምን አይነበብም?

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መምህርና ሐኪም የሆት ዶ/ር ናሆም ግሩም ''የእኔ እጅ ጽሑፍ ስለሚነበብ እንደ ሐኪም የማያዩኝ ሰዎች አሉ'' አሉን።

ቆይ ቆይ ዶክተር በቅድሚያ አንድ ህመምተኛ ወደ ሐኪሙ ዘንድ ከገባበት እና ወንበር ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ አቀርቅራችሁ በሽተኛው የተነፈሰውን ሁሉ የምትጽፉት ለምንድን ነው? አልናቸው።

የተለያዩ ሰዎች ሊስማሙበት ባይችሉም እንኳን ከሥራ መስኮች መካከል እንደ ሀኪሞች የሚጽፍ የለም አሉን። "ጋዜጠኞችስ ዶክተር?" የኛ ጥያቄ ነው።

በፈገግታ ታጅበው፤ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ሐኪም ለህመምተኛው ሕክምና ካደረገ በኋላ የሠራቸውንና የተነጋገራቸውን በሙሉ መዝግቦ በታካሚው መዝገብ ላይ ማስቀመጥ ስላለበት ነው ሲሉ አብራሩ።

''ለበሽተኛው አገልግሎት ሲሰጥ የዋለ፤ የተነጋገረውን የሕክምና አገልግሎት በአግባቡ መዝግቦ ካላስቀመጠ አገልግሎት እንዳልሰጠ ይቆጠራል''

በቀን ለ50 ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ ሐኪም፤ የ50 ታካሚ ታሪክ ሲጽፍ ይውላል ማለት ነው።

ደራሲ ቢሆኑ ስንት መጽሐፍ ይወጣው ይሆን? የኛ ሃሳብ ነው።

ዶ/ር ናሆም ሙያዊ ማብራሪያቸውን ይቀጥላሉ፤ ከዚህም በተጨማሪም ''በብዛት በጻፍን ቁጥር በጣቶቻችን ላይ የሚገኙ ጥቃቅን ነርቮች ስለሚደክሙ እንዳይነበብ ሆኖ ሊጻፍ ይችላል'' ካሉ በኋላ በተመሳሳይም በፍጥነት መጻፋ ራሱ የሐኪሞቹ የእጅ ጽሑፍ በቀላሉ እንዳይነበብ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ይጠቀሳል አሉን።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ አንድ ዶክተር በርካታ ሕሙማንን በሚያክምበት አገር የእያንዳንዱን ታካሚ ታሪክ መመዝገብ የግድ መሆኑን ይናገራሉ።

ደግሞ ወረፋ በበዛበት ወቅት አንዱን ህመምተኛ ካከመ በኋላ ሌላኛውን ለማከም ጥድፊያ ይኖራል። የእጅ ጽሑፍ ደግሞ እንኳንስ ተጣድፈውበት እንዲሁም ሆደ ባሻ ነው።

ዶ/ር ናሆምም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ፤ ''ከዚህ የተነሳ ነው የሐኪሞች እጅ ጽሑፍ የማይነበብ ወይንም የማያምር የሚሆነው ይሆናሉ'' በማለት።

ለዶ/ር ናሆም ያቀረብነው ሌላ ጥያቄ የሐኪሞች እጅ ጽሑፍ ለምንድን ነው ከዘርፉ ባለሙያዎች ውጪ የማይነበበው?

"የሕክምና ሳይንስ ራሱን የቻለ የሙያ ቋንቋና ቃላት ስላሉት ሰዎች እኛ የምንጽፈውን ጽሑፍ በትክክል ማንበብ የማይችሉ ይመስላቸዋል እንጂ የጤና ባለሙያ ማለትም ነርሶችና ፋርማሲስቶች በቀላሉ ሊያነቡት ይችላሉ።"

በተጨማሪም ይላሉ ዶ/ር ናሆም፤ ሀሳባቸውን ሲያብራሩ፤ የሕክምና ሳይንስ በአጭርና በአህጽሮተ ቃላት የሚገለጹ ብዙ አባባሎች ስላሉት ሐኪም የጻፈውን ጽሁፍ ማንበብ ሊያስቸግር ይችላል አሉን።

ለዚህ ማስረጃ ፈለግን፤ እርሳቸውም ለምሳሌ ካሉ በኋላ BID የሚለው አጽህሮተ ቃል ይህንን መድሀኒት በቀን ሁለት ጊዜ ይውሰዱ የሚል አገላለጽን ይተካል አሉን፡፡

"ህመምተኛ ስለ በሽታው የማወቅ ሙሉ መብት አለው"

ታካሚዎች ስለ በሽታቸው፣ ስለታዘዘላቸው መድሃኒትና፣ የምርመራቸውን ውጤት ለማወቅ የመጀመሪያዎቹና ባለ ሙሉ መብትም ናቸው ይላሉ ዶ/ር ናሆም።

ይሁን እንጂ የሕክምና ሙያ ያላቸው ራሳቸው የሐኪሞች የእጅ ጽሑፍ ሳይነበባቸው ቀርቶ የመድሃኒት ማዘዣ ተመልሶ ወደ ዶክተሩ የሄደበት ጊዜ መኖሩን ያስታውሳሉ።

አንድ ሌላ ገጠመኛቸውን ጨመሩልን። "ሐኪም መጥቶ እስኪያነብላቸው ድረስ ታካሚው መድሀኒት ሳይወስድ የቆየበት ጊዜ አውቃለሁ" አሉን።

የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ ማለት እዚህ ጋር ነው. . .

እንደው ለመሆኑ የዶክተሮች እጅ ጽሑፍ ላይ የተሠራ ጥናት ይኖር ይሆን?

በሕንድ አገር የሀኪሞች እጅ ጽሁፍ በትክክል መነበብ ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ 60 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን በአገሪቱ የተሠራ ጥናት ያሳያል አሉን።

በእኛ አገርስ ቢሠራ ታዲያ ምን ውጤት ይገኝ ይሆን? ሌላ ጥያቄ እናንሳ፤ ከሕክምና ሥነ ምግባር አንጻርስ የእጅ ጽሑፍ እንዴት ይታያል?

"የሕክምና ሳይንስ ሥነ ምግባር አንድ ሐኪም የሚጽፋቸው ጽሑፎች ሁሉም ሰዎች በሚያነቡት መልኩ እንዲሆን ያዛል" በማለት መልስ ሰጥተውናል።

እኛም እንደ ሐኪም በዚህ እናምናለን ብለው "ሌሎቹንም እንዲሁ እንመክራለን" ብለዋል ዶክተሩ።

በምዕራባውያኑ አሰራር አንድ ታካሚ ስለ ጤና እክሉ አንብቦ እንዲረዳ በኮምፒውተር ተጽፎ ይሰጠዋል። በኢትዮጵያ ግን ከህመምተኞች ቁጥርና ካለው መዋቅር የተነሳ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ጽፎ ማዘጋጀት አስቸጋሪ ነው ይላሉ ዶ/ር ናሆም።

አንዳንድ ሰዎች በህክምና ትምህርት ዓመት መጨረሻ አካባቢ ሲደርሱ "ሐኪሞች የእጅ ጽሑፍ ኮርስ ይሰጣችኋል?" በማለት ይጠይቃሉ ያሉት ዶ/ር ናሆም፤ በሕክምና ትምህርት ውስጥ ስለእጅ ጽሑፍ የሚሰጥ ትምህርት እንደሌለ ይገልጻሉ።