ደቡብ አፍሪካ፡ ታዳጊዎች ሲገረዙ የሞቱባቸው ትምህርት ቤቶች ታገዱ

ታዳጊዎች ሲገረዙ የሞቱባቸው ትምህርት ቤቶች ተዘጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታዳጊ ወንዶች ሲገረዙ ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ በርካታ ባህላዊ ትምህርት ቤቶችን አገደች።

የአገሪቱ የሀይማኖትና ባህል ኮሚሽን፤ ቢያንስ 20 ታዳጊዎች ለመሞታቸው ተጠያቂ ናቸው ያላቸው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ጠይቋል።

ታዳጊ ወንዶች ለሳምንታት በተራራማ አካባቢ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ የሚያደርጉት ትምህርት ቤቶች፤ ታዳጊዎች ወደ ወጣትነት የሚሸጋገሩባቸው እንደሆኑ ይነገራል።

በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እድሜያቸው ከ15 እስከ 17 የሚደርሱ ወንዶች፤ ጫካ ውስጥ ተገልለው እንዲቆዩ ተደርጎ፤ እንዴት በማኅበረሰቡ ዘንድ ሁነኛ ሰው መሆን እንደሚችሉ እንደሚማሩ ይነገራል። ሆኖም ግን በነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ምን እንደሚከናወን በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም።

'ኡኩዋላኩዋ' የሚባለው ሂደት ከታዳጊነት ወደ ወጣትነት ለመሸጋገር አስፈላጊ መሆኑን እንደ ቋሳ እና ንዴቤሌ ያሉ ጎሳዎች ያምናሉ። ታዳጊዎች ከባህላዊ ትምህርት ቤቶቹ ሲወጡም ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል።

በነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሕይወታቸውን ያጡ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እንዲሁም በግርዛት ወቅት ጉዳት የገጠማቸው ታዳጊዎችም አሉ።

አምና በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች በብልታቸው ላይ በደረሰባቸው ጉዳት ሳቢያ እንዲሁም በቂ ውሀ ባለማግኘት ወደ ህክምና መስጫዎች ተወስደው ነበር።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ግርዛት የሚካሄደው ታዳጊዎች ከትምህርት እረፍት በሚወስዱባቸው ወራት ነው። ከ15 እስከ 17 እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ታዳጊዎች በባህላዊ የቀዶ ህክምና ባለሙያ አማካይነት ይገረዛሉ። ታዳጊዎቹም ስለ ግርዛቱ ምንም እንዳይናገሩ ተደርጎ ሂደቱ በሚስጥር ይከናወናል።

እአአ ከ2012 ወዲህ ወደ 400 ታዳጊዎች ከግርዛት ጋር በተያያዘ ሞተዋል። አብዛኞቹ ታዳጊዎች የሚሞቱት በቂ ውሀ ባለማግኘት፣ ቁስላቸው ስለሚያመረቅዝና ተገቢውን ህክምና ስለማያገኙ ነው።

አንዳንዶች ሂደቱን ኋላ ቀር እና አደገኛ ቢሉትም፤ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት የትኛወም ማኅበረሰብ ባህሉን እንዲያስቀጥል ይፈቅዳል።

ባህላዊ ትምህርት ቤቶቹ በመንግሥት የሚታወቁ ሲሆኑ፤ አሁን ላይ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ሀኪሞች ትምህርት ቤቶቹን እንዲጎበኙ እየከፈለ ነው። በመንግሥት ያልተመዘገቡ ትምህርት ቤቶችን መፈተሽ ግን አስቸጋሪ ነው።

መንግሥት የሚደግፋቸው ጤና ጣቢያዎች የግርዛት አገልግሎት በመስጠት ሰዎች ከባህላዊ መንግድ ውጪ አማራጭ እንዲኖራቸው ለማድረግ ቢሞክሩም፤ የምዕራባውያን ባህል አራማጆች እንደሆኑ የሚያምኑ አሉ።