አካል ጉዳተኛዋና የመብት ተሟጋቿ ሞዴል ማማ ካክስ በሰላሳ አመቷ አረፈች

ማማ ካክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አካል ጉዳተኛዋና የመብት ተሟጋቿ ሞዴል ማማ ካክስ በሰላሳ አመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

የዘር ግንዷ ከሃይቲና አሜሪካ የሚመዘዘው ሞዴሏ ወደ ለንደን ባቀናችበት ወቅት አሟት እንደነበር ቤተሰቦቿ በኢንስታግራም ገፃቸው አስታውቀዋል።

ካክስሚ ብሩተስ ወይም በቅፅል ስሟ ማማ ካክስ የምትታወቀው ሞዴሏ ታዳጊ እያለች አንድ እግሯን በሳንባና በአጥንት ካንሰር አጥታለች፤ ሙሉ ህይወቷንም ለጥቁር ሴቶች በተለይም በፋሽኑ አለም ውስጥ ስላሉ አካል ጉዳተኞች ስትታገል ቆይታለች።

"ካክስ ታጋይ ነበረች ማለት ያደረገችውን ትግል ያሳንሰዋል" በማለት ቤተሰቦቿ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

"ከካንሰር እንደተረፈ ሰው በህይወቷ በሙሉ ለችግሮች እጇን ያልሰጠች፤ እክሎችን ስትጋፈጥ የኖረችና በአሸናፊነት የኖረች ሰው ናት፤ እስከ መጨረሻ እስትንፋሷም ይህንኑ ቀጥላበት ነበር" ብለዋል።

ካክስ እውቅናን ያተረፈችው ስለ አካል ጉዳተኝነት፣ ፋሽን፣ ጉዞ በምትፅፋቸው ፅሁፎች ሲሆን፤ በተለይ ፅሁፎቿ ላይ የሚንፀባረቀው እውነተነኝነት ብዙዎችን ያስደመመ ነበር።

ምንም ሳትሸማቀቅበትም ሰው ሰራሽ እግሯን በማሳየትና በማስጌጥ የምትነሳቸው የጎዳና ላይ ፎቶዎች የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዚህ አመትም 'ዴዝድ ኤንድ ኮንፊውዝድ' ለተባለው መፅሄት በሰጠችው ቃለ መጠይቅ "ሰው ሰራሽ እግሬ የማፍርበት ሳይሆን እንደ አንድ የጥበብ ስራ የምመለከተው ነው" ብላለች።

ባለፉት ጥቂት ዓመታትም ቮግን ጨምሮ ታዋቂ በሆኑ የፋሽን መፅሄቶች ላይ መውጣት ችላለች።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሲፎራ፣ አሶስና ቶም ሂል ፊገርስ የመሳሰሉ ጥር የልብስና ቁሳቁስ አምራች ኩባንያዎች ሞዴል ነበረች።

በዚሁ አመትም ለኒውዮርክ ፋሺን ሳምንት፣ እንዲሁም የታዋቂዋ ዘፋኝ ሪሃና ኩባንያ ለሆነው ሳቬጅ ኤክስ ፌንቲ ሌብልን ወክላ መድረክ ላይ ታይታለች።

ህልፈተ ዜናዋን ተከትሎ ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሃዘናቸውን የገለፁ ሲሆን ሪሃናም "እህቴ በሰላም እረፊ፤ በቁንጅና የተሞላሽ ኃያል ነበርሽ" ብላለች።