በእንግሊዝ ከዕፀ ፋርስ የተሰራው የሚጥል በሽታ መድኃኒት ገበያ ላይ ሊውል ነው

ከዕፀ ፋርስ የተሰራው መድኃኒት

የፎቶው ባለመብት, Handout

በሚጥል በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ ለሚሰቃዩ ሰዎች መፍትሄ ስለሚያስገኝ መድኃኒት ከወደ እንግሊዝ ተሰምቷል፤ ይህም ከዕፀ ፋርስ (ማሪዋና) የተሰራ ነው።

የሃገሪቱን የመድሃኒት ጥራትና ደህንነት የሚቆጣጠረው 'ኤንኤችኤስ' ተቋም ዶክተሮች ከታህሳስ 27፣ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለህሙማን ማዘዝ እንደሚችሉ አስታውቋል።

መድኃኒቱ ዕድሜያቸው ከሁለት አመት ጀምሮ ለሆኑ ህፃናት እንዲሁም ለአዋቂዎች ጥቅም ላይ መዋል ይችላል ተብሏል።

ለዕፀ ፋርስ መደኃኒነትነት ሲሟገቱና ሲጎተጉቱ የነበሩ በበኩላቸው "አርፍዳችኋል" እያሉ ነው።

የህክምና ሙከራዎች እንደሚያሳዩት ከዕፀ ፋርስ የተሰራ የሚዋጥ ክኒን የወሰዱ ህፃናት ማንቀጥቀጡ አርባ በመቶ እንደቀነሰላቸው ነው።

መድኃኒቱ 'ሌኖክስ ጋስታውት ሲንድሮም' እና 'ድራቬት ሲንድሮም' ለተሰኙ ሁለት አይነት ለሚጥሉ የበሽታ አይነቶች የሚውሉ ይሆናል። በሽታዎቹ በክፉኛ መንገድ ህፃናትን የሚያጠቁ ሲሆን በቀን ውስጥም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማንቀጥቀጥ የሚያስከትሉ ናቸው።

ዜናው በዘርፉ ላይ የተሰማሩትን ያስፈነደቀ ሲሆን 'ኤፕለፕሲ አክሽን' የተባለ ድርጅት ስራ አስፈፃሚ ፊሊፕ ሊ "ተስፋን የሚያሰንቅ ጉዳይ ነው፤ የብዙዎችን ህይወት ይቀይራል" ብለዋል።

ነገር ግን ይህ 'ኤፒድዮሌክስ' የሚል ስያሜ የተሰጠው መድኃኒት አልጋ ባልጋ እንዳልሆነና፤ ከዕፀ ፋርስ የተሰሩ ለሌሎች በሽታዎች የሚያገለግሉ መድኃኒቶችንም ፈዋሽነት እንደ ማስረጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በዕፀ ፋርስ ፈዋሽነት ላይ የሚሰራው 'ሜዲካል ካናቢስ' አስተባባሪ ፒተር ካሮል በበኩላቸው "ትንሽ ረፍዷል" በማለት ለመድኃኒትነት የሚውለው ዕፀ ፋርስ (ማሪዋና) 'ሲቢዲ' እና 'ቴትራሃይድሮካናቢኖል' የተባሉ ንጥረ ነገሮችን እንዲያካትት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቢቢሲም ባናገራቸው ወቅት "በከፍተኛ ሁኔታ በሚጥል በሽታ ለሚሰቃዩ ህፃነት 'ሲቢዲ' የተባለው መድኃኒት ትንሽ መጠን ካለው 'ቴትራሃይድሮካናቢኖል' ንጥረ ነገር ጋር ሲሰጥ ፈዋሽነቱ ከፍተኛ ቢሆንም ሁለቱም ንጥረ ነገሮች በእንግሊዝ ፈቃድ የላቸውም" ብለዋል።

አክለውም ምንም እንኳን ባለፈው ዓመት ህጉ ተቀይሮ የተመረጡ ዶክተሮች ለመድኃኒትነት የሚውለው ዕፀ ፋርስ ከ 'ሲቢዲ' እና 'ቴትራሃይድሮካናቢኖል' ንጥረ ነገሮች ጋር ማዘዝ ቢችሉም አሁንም ንጥረ ነገሮቹ ፈቃድ የላቸውም።

"ምንም እንኳን ህጉ ቢቀየርም በሚያስደነግጥ ሁኔታ ሁለቱን ንጥረ ነገሮች የያዘ የእፀ ፋርስ መድኃኒት እስካሁን አልታዘዘም" ብለዋል።

'የኤንኤችኤስ' ስራ አስፈፃሚ ሲሞን ስቲቨንስ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ለገበያ መዋሉን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ህመምተኞች መድኒቱን ለማግኘት እንደሚችሉና ህይወታቸውም እንደሚቀየር ተናግረዋል።