ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኢትዮጵያ ውስጥ ደብዛው የጠፋው ኤርትራዊው ኤርሚያስ ምርመራ እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጠ

ኤርምያስ ተኪኤ

የፎቶው ባለመብት, ISAIAS TEKIE

ከሁለት አመታት በፊት ከስዊድን አዲስ አበባ በገባ በሁለት ሳምንቱ ደብዛው ጠፋ የተባለው ኤርትራዊ ስዊድናዊው ኤርሚያስ ተክኤን አስመልክቶ የጠቅላይ አቃቤ ህግ የምርመራው ጉዳይ በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሲል መመሪያ መስጠቱን በስዊድን የኤርሚያስ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሙሴ ኤፍሬም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ይህንን መመሪያ ያስተላለፈው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በላከው ደብዳቤ ነው።

ሕዳር 3/2012 ዓ.ም የተፃፈውን ደብዳቤ ቢቢሲ ማግኘት የቻለ ሲሆን ምርመራው ተመዝግቦ በሂደት ላይ የሚገኝ ከሆነ ከሚመለከታቸው የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች በጋራ በመሆን የተጀመረው ምርመራ በተቻለ ፍጥነት የሚጠናቀቅበትና፤ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲከናወን ብሏል።

አቶ ሙሴ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የሰጠው መመሪያ ዓርብ ዕለት ታህሳስ 10/2012 ዓ.ም እንደደረሳቸው ገልጸው፤ ይህም ሁኔታ ትልቅ ተስፋ እንደሰጣቸው አክለዋል።

"እስካሁን ባለው የሃገሪቷን ህግ ተከትለን ስንሄድ ነበር። ይሁን እንጂ ከአሁን በኋላ የምናየው ለውጥ ከሌለ ትዕግስታችን በማለቁ ወደ አፍሪካ ህብረት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አቤቱታ እናቀርባለን" ብለዋል።

የኤርሚያስ ተኪኤ ቤተሰቦችና ጠበቆች፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተሻለ የምርመራ እውቀትና ክህሎት ያላቸው የመርማሪዎች ቡድን በማደራጀት ምርመራውን በጥልቀትና በፍጥነት እንዲካሄድ የስራ መመሪያ ይሰጥልን ብለው በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም አመልክተው ነበር።

ኤርትራዊ -ስዊድናዊ ኤርሚያስ ተኪኤ ማን ነው?

ኤርሚያስ ትውልዱ ኤርትራዊ ሲሆን ዜግነቱ ደግሞ ስዊድናዊ ነው።

ኤርሚያስ አዲስ አበባ የገባው ሚያዝያ 26፣ 2010 ዓ.ም ሲሆን፤ አዲስ አበባ በሚገኘው አርክ ሆቴል እስከ ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም ቆይቷል ።

ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ አራት ሰዓት ሲሆን ዳህላክ (ኤፍሬም) የተባለ ግለሰበብ ጠርቶት በመኪና ከወሰደው በኋላ ደብዛው መጥፋቱን ቤተሰቡና ጠበቆቹ ማሳወቃቸውን የጠቅላይ አቃቤ ህግ ደብዳቤ ያስረዳል።

ጉዳዩንም ለማጣራት ወዳረፈበት ሆቴል መሄዳቸውን ጠቅሰው ከሆቴሉ ያገኙትንም መረጃ ይዘው ሰኔ 22፣ 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ክፍል ምርመራ እንዲጣራላቸው አመልክተው፤ ምስክርነት ሰጥተው ቢመለሱም እስካሁን ድረስ ያለበትን እንደማያውቁና ደብዛው እንደጠፋ ባቀረቡት አቤቱታ መግለፃቸውን ይኸው የጠቅላይ አቃቤ ህግ ደብዳቤ ያስረዳል።

አስመራ ተወልዶ ያደገው ኤርሚያስ ባለትዳር ሲሆን በስዊድን አገር በስደት ከ12 ዓመታት በላይ ኖሯል።

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ በሚል ስዊድን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቪዛ ጠይቆ፤ ኤምባሲው በሰጠው ፍቃድ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል።

ኤርሚያስ፤ ከዚህ ቀደምም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እንደነበር ቤተሰቦቹ ለቢቢሲ ገልጸዋል።