ኩባ ከ 43 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑኤል ማሬሮ ክሩዝ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ ካነል በሀገሪቱ ታሪክ ከ 43 ዓመታት በኋላ የቀድሞውን የቱሪዝም ሚኒስትር ማኑኤል ማሬሮ ክሩዝን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል።

የወቅቱ የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1976 የጠቅላይ ሚኒስትር ቦታ አላስፈላጊ ነው ብለው ነበር ያስቀሩት።

በአዲሱ ሕገ መንግስት መሰረት ደግሞ ይህ ሀላፊነት ተመልሶ እንዲመጣ ባለፈው ዓመት ተወስኖ ነበር።

የ 56 ዓመቱ ማኑኤል ማሬሮ በፕሬዝዳንቱ ትከሻ ላይ የነበሩ ሀላፊነቶችን ቀስ በቀስ ተረክበው ስራቸውን እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን አንዳንድ ተቺዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት ለታይታ ነው እንጂ ዋናው ስልጣንና ውሳኔ የማስተላለፍ አቅም ያለው የኩባ ኮሙኒስት ፓርቲ እና ወታደሩ እጅ ላይ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑኤል ማሬሮ ለኩባ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኘው የቱሪዝም ዘርፍ መምጣታቸው ዘርፉን ለማሳደግና ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ሊከፍቱ እንደሚችሉም ተገምቷል።

ማኑኤል ማሬሮ በአውሮፓውያኑ 2000 በፊደል ካስትሮ የሀገሪቱ ቱሪዝም ምኒስትር ተደርገው ተሹመዋል። በእሳቸው ዘመንም የቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃትን አሳይቷል።

የቱሪዝም ሚኒስትርነቱን ቦታ ማን እንደሚይዘውም እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ ካነል ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመረጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ ከበፊት ስራቸው ጋር በተያያዘ ማኑኤል ማሬሮ በተለይ ከውጭ ኢንቨስተሮች ጋር ጥሩ የሆነ ግንኙነት መፍጠር ይችላሉ ብለዋል።

''ግልጽነቱ፣ ስራውን በአግባቡ መስራቱ እንዲሁም ለኮሚዩኒስት ፓርቲውና ለአብዮቱ ያለው ታማኝነት በጣም አስገራሚ ነው'' ብለዋል ፐሬዝዳንቱ።