ኒውዝላንዳውያን 56 ሺ የጦር መሳሪያዎችን ለመንግሥት አስረከቡ

የተመለሱት መሳሪያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ኒውዝላንዳውያን ከ 56 ሺ በላይ የሚሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ለመንግሥት እንዳስረከቡ ፖሊስ ገልጿል።

መንግሥት ለመሳሪያዎቹ ካሳ የሚከፍል ሲሆን ግማሽ አውቶማቲክ የሆኑ የጦር መሳሪያዎች በሀገሪቱ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አግዶ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ በክራይስት ቸርች በሚገኙ ሁለት መስጂዶች ላይ በተፈጸመው ጥቃት 51 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ነው።

እገዳው በወርሃ መጋቢት ከተከሰተው ጥቃት ሳምንታት በኋላ በፓርላማው የጸደቀ ሲሆን በኒውዝላንድ ዘመናዊ ታሪክ እጅግ ከባዱ ነበር ተብሏል።

ጥቃቱን የፈጸመው አውስትራሊያዊው የነጮች የበላይነት አቀንቃኝ ብሬንተን ታራንት በቁጥጥር ስር ውሎ የፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል።

ባሳለፍነው ዓመት ሚያዝያ ላይ የተጀመረው የሀገሬውን ዜጎች መሳሪያ መሰብሰብ ባለፈው ሳምንት የተጠናቀቀ ሲሆን ዜጎች ለመሳሪያዎቹ እስከ 95 በመቶ የሚደርስ ካሳ ተከፍሏቸዋል።

የፖሊስ ሚኒስትሩ ሰቱዋርት ናሽ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ''ከ 56 ሺ በላይ የሚሆኑ መሳሪያዎችን ከማህበረሰቡ መሰብሰብ ችለናል፤ ይሄ ጥሩ ነገር ነው ብለን እናምናለን'' ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2016 የኒውዝላንድ ፖሊስ ሰበሰብኩት ባለው መረጃ መሰረት በሀገሪቱ 1.2 ሚሊየን ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች በዜጎች እጅ ላይ ይገኛሉ። አብዛኛዎቹ መሳሪያዎች ደግሞ ለአደን የሚውሉና ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ ናቸው።

በክራይስት ቸርች ምን ተፈጠረ?

መጋቢት 6 2011 ብሬንተን ታራንት በክራይስት ቸርች አል ኑር መስጂድ እና ሊንዉድ ኢስላማዊ ማዕከል ውስጥ ጥቃት ፈጸመ።

በጥቃቱም 51 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 40 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሰባቸዋል። አውስትራሊያዊው ብሬንተን በፖሊስ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በነብስ ማጥፋት፣ በመግደል ሙከራና በሽብር ክስ ቀርቦበታል።

ግለሰቡ እስካሁንም ድረስ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሎ እየተከራከረ የሚገኝ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ብያኔ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።