ሱዳን የዳርፉር ግጭት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችን መመርመር ጀመረች

አል በሺር Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የሱዳን የቀድሞ ፕሬዝዳንት በቀረበባቸው የሙስና ክስ የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል

ሱዳን በቀድሞ ፕሬዝዳንቷ ኦማር አል በሺር በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ዳርፉር ላይ የተፈፀመውን ወንጀል መመርመር ጀመረች።

የችሎት ሂደቱ ከሱዳን ውጪ እንደሚካሄድ አቃቤ ሕጉ ታገልሲር አል ሄበር ተናግረዋል።

ከአስር ዓመት በፊት የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዳርፉር ለተፈፀመው የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በበሺር ላይ የእስር ማዘዣ ቆርጦባቸው ነበር።

የኦሮሞና የሶማሌ ግጭት የወለደው የቴሌቭዥን ጣቢያ

በዳርፉር በታጣቂዎችና በሱዳን መንግሥት ደጋፊ ጦሮች መካከል ውጊያ የተጀመረው በጎርጎሳውያኑ 2003 ነበር። እንደተባበሩት መንግሥታት ከሆነ በዚህ ግጭት 300ሺህ ሰዎች ሞተዋል።

አቃቤ ሕግ ሄበር እንዳሉት ከሆነ፣ የዳርፉር ምርመራ የሚያተኩረው " የቀድሞ ባለስልጣናት" ላይ ሲሆን በስም እነማን ናቸው የሚለውን ከመናገር ተቆጥበዋል።

ነገር ግን ማንም ከምርመራው ላይ እንዳይካተት አይደረግም ሲሉ አስታውቀዋል።

በዳርፉር የተፈፀሙ ሁሉንም ወንጀሎች እንደሚመለከቱ ገልፀው፣ ይህም በርካታ ግድያዎችና ደፈራዎችንም እንደሚጨምር አስታውቀዋል።

አስፈላጊ ከሆነ ምርመራው ከሀገር ውጪ ሊካሄድ ይችላል ያሉት ሚስተር ሄበር፣ ይህም አል በሺር ጉዳያቸው ወደ አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሄግ ፍርድ ቤት ሊዘዋወር ይችላል ለሚለው ፍንጭ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ ለምን ይጠቅማታል?

30 ዓመት በስልጣን ላይ የቆዩት የሱዳን የቀድሞ ፕሬዝዳንት አል በሺር በሀገሪቱ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ ከስልጣን መውረዳቸው ይታወሳል።

ሱዳን በአሁኑ ሰአት ከወታደራዊ መሪዎችና የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ይመሩ ከነበሩ አካላት በተውጣጣ የሽግግር መንግሥት እየተመራች ትገኛለች።

አል በሺር ከስልጣን ከወረዱ በኋላ የአለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቢያነ ሕግጋት በሺር በዳርፉር ለተፈፀመው ወንጀል ችሎት ፊት ቀርበው ጉዳያቸው እንዲታይ ጠይቀው ነበር።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት በዳርፉር ግጭት 300ሺህ ሰዎች ሲሞቱ 2ሚሊየን ሰዎች መፈናቀላቸውን ይናገራል

አል በሺር ከስልጣን እንደወረዱ ስልጣን ላይ የወጣው ወታደራዊ መንግሥት ጥያቄውን ውድቅ አድርጎት የነበረ ሲሆን የሱዳንን ሕዝባዊ አመጽ የመራውና በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው አካል ግን አልበሺር ተላልፈው ቢሰጡ ችግር እንደሌለበት አስታውቋል።

ሚስተር ሄበር የአል በሺር ፍራቻ የቀድሞ ደህንነት ኃላፊያቸው ሳላህ ጎሽ ላይ ምርመራ ይደረጋል የሚለው ነው ብለዋል።

እኚህ የሀገሪቱ የደህንነት ኃላፊ አል በሺር ከስልጣን በወረዱ በሁለት ቀናት ውስጥ ነው ከስልጣን የለቀቁት።

የትግራይና የፌደራል መንግሥቱ ግንኙነት በጣም አሳሳቢ ነው- ዶ/ር አብረሃም ተከስተ

" በሳላህ ጎሽ ላይ እየተደረገ ባለው አራት ምርመራዎች የተነሳ ኢንተርፖል ይዞ ወደ ሱዳን እንዲያመጣቸው እየሰራን ነው" ብለዋል።

በዳርፉር የጃንጃዊድ ሚሊሺያ ኃላፊ የነበሩት ሞሀመድ ሀምዳን "ሄሜቲ" ዳጎሎ ምርመራ እየተደረገባቸው ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።

ግለሰቡ በሱዳን ተቃውሞ እያደገ ሲሄድ ፊታቸውን ከአል በሺር አዙረው ከተቃዋሚዎቹ ጋር አብረው ነበር።

ከዚያ በኋላ ነው የሱዳን ሽግግር ወታደራዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት። በኋላም ቢሆን የሱዳንን የሲቪል አስተዳደር የሚመራውን የሽግግር መንግሥት የሚከታተለው ምክር ቤት አባል ናቸው።

የሱዳንን መፃዒ ዕድል የሚወስኑት የጦር አበጋዝ

ሂይውመን ራይትስ ዎች ግን በተለያያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች ይከስሳቸዋል።

ሄሜቲ በዳርፉር ሲቪሎችን ለመከላከል ኃይል መጠቀም አስፈላጊ ነው ብለው ይከራከሩ ነበር።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አልበሺር በተከፈተባቸው የሙስና ክስ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የሁለት ዓመት እስር እንደተፈረደባቸው ይታወሳል።

አቃቢያነ ህግጋት በሱዳን በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ በተገደሉ ሰዎች ዙሪያ ምርመራ እያደረጉባቸው ሲሆን ወደ ስልጣን ያመጣቸው መፈንቅለ መንግሥትንም በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ ነው ተብሏል።