ቱርክ ከዚህ በኋላ ከሶሪያ የሚመጡ ስደተኞችን አልቀበልም አለች

የሶሪያ ስደተኛ እናት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ከዚህ በኋላ ሀገራቸው አዲስ የሚመጡ የሶሪያ ስደተኞችን ማስተናገድ እንደማትችል ገለጹ።

ምንም እንኳን የቱርክ ድንበር አካባቢ ከበድ ያለ ጥበቃና በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ በምታዋስነው ኢድሊብ ግዛት በኩል የአይኤስ ታጣቂዎች ቢኖሩም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያንን ወደ ቱርክ ከመሰደድ አላስቆማቸውም።

ቱርክ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት 3.7 ሚሊዮን የሶሪያ ስደተኞችን የተቀበለች ሲሆን በዓለማችን ከፍተኛው ቁጥር ነው።

ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን እንዳሉት አዲሱ የሶሪያውያን ስደተኞች እንቅስቃሴ ከሀገራቸው አልፎ መላው አውሮፓን የሚያቃውስ ነው።

በአማጺያንና ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድን የሚቃወሙ አክራሪ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱባት ኢድሊብ ግዛት እስከ ሶስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሶሪያውያን የሚኖሩ ሲሆን መጨረሻቸው እስካሁን አልታወቀም።

'' ከ 80 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከኢድሊብ አቅጣጫ ወደ ቱርክ ድንበር መጥተዋል። እነዚህ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጭካኔ የማይቆም ከሆነ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ይጨምራል። ቱርክም ብትሆን ተጨማሪ ስደተኞችን የማስተናገድ አቅም የላትም'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ ።

ቱርክ እንደ አማራጭ የምታቀርበው ደግሞ ሶሪያ ውስጥ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ከኩርድ ኃይሎች ባስለቀቀችው ነጻ ቀጠና ውስጥ ስደተኞቹ እንዲሰፍሩ ነው።

ፕሬዝዳንቱ ይህ የማይሆነ ከሆነ እና የአውሮፓ ሀገራት አፋጣኝ መፍትሄ የማያቀርቡ ከሆነ ግን ቱርክ ሁሉም የሶሪያ ስደተኞች ወደ አውሮፓ አልፈው እንዲገቡ በሯን እንደምትከፍትላቸው አስጠንቅቀዋል።