ስልካችንን በማናውቀው ቦታ 'ቻርጅ' ማድረግ ምን ጉዳት አለው?

ቻርጅ ማድረጊያ ሶኬት Image copyright Getty Images

ተንቀሳቃሽ ስልክዎ ወይም ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚጠቀሙበት ታብሌት ባትሪ ሲጨርስ ምን ያደርጋሉ? ዘመናዊውን ሰው ከሚያስጨንቁት ትልልቅ ነገሮች መካከል የስልኮች ባትሪ መጨረስ አንዱ እየሆነ መጥቷል።

ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች በተለይም በሆቴሎች፣ የስብሰባ ቦታዎች፣ አየር ማረፊያዎች እና በመሳሰሉት ስፍራዎች ቻርጅ ማድረጊያ ሶኬቶችን ማዘጋጀት በአሁኑ ወቅት እየተለመደ መጥቷል።

ነገር ግን የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሁሉም ሰው በሚጠቀምባቸው ቻርጅ ማድረጊያዎች ስልኮትን ወይም ታብሌቶችን ቻርጅ ማድረግ ለተለያዩ ስልክ ጠላፊዎችና ጥቃቶች ሊያጋልጥ ይችላል።

ሞዛምቢክ ከሞባይል ላይ መረጃ የሚወስዱ ሰዎችን በእስር ልትቀጣ ነው

ሞባይል ስልክዎ ላይ መከራን አይጫኑ

ሕዝብ በብዛት ወደሚጠቀምባቸው ማዕከላት አዘውትረው የሚመጡ የስልክ ጠላፊዎች ቻርጅ ማድረጊያ ገመዶችን ቀድመው በማዘጋጀት ከስልክዎ፣ ከታብሌትዎ አልያም ከላፕቶፕዎ በርካታ መረጃዎችን ሊሰርቁ ይችላሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ጠላፊዎች ሴራቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች ከየትኛውም ቦታ እጅግ ቀላል በሆነ መልኩ መገኘት የሚችሉ ናቸው። ይህ ደግሞ ማንኛውም ሰው ሊያደርገው የሚችለው እንደሆነ ያሳያል።

ተጠቃሚዎች አገር ሰላም ብለው ስልካቸውን ቻርጅ ሲያደርጉ በጎን በኩል ግን ስልኮቻቸውን የሚሰልሉ መተግበሪያዎችና ሶፍትዌሮች አብረው ይገባሉ።

Image copyright Getty Images

በርካታ ሰዎች ደግሞ ቻርጅ ማድረጊያ ገመዶችን ይዘው ስለማይንቀሳቀሱ እነዚህ ጠላፊዎች በሶኬቶቹ ላይ ገመዶችን እስከማስቀመጥ ይደርሳሉ። የተቸገሩ ሰዎች ደግሞ ተገላገልን ብለው ባገኙት ገመድ ቻርጅ ያደርጋሉ።

በዚህም በቀላሉ በጠላፊዎች ወጥመድ ውስጥ ወደቁ ማለት ነው።

ምንም እንኳን በጠላፊዎች በብዛት የሚጠቁት ዴስክቶፖችና ላፕቶፖች ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ታብሌቶች የዚሁ ጥቃት ሰለባ መሆነ ጀምረዋል።

በሞባይልዎ የኢንተርኔት ወጪ ተማረዋል?

የበይነ መረብ መረጃ ደህንነት ላይ የሚሰራው ካስፐርስኪ የተባለው ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት በአውሮፓዊያኑ 2018 ብቻ 116. 5 ሚሊዮን ሰዎች ስልኮቻቸው ተበርብረው መረጃ ተሰርቆባቸዋል። በ2017 ግን ቁጥሩ ወደ 66.4 ሚሊዮን ወርዶ የነበረ ሲሆን ይህም አሃዙ ምን ያህል እንደጨመረ ማሳያ ነው።

ይኽው ድርጅት አክሎም ነዋሪነትዎ በእስያ፣ መካከለኛ ምሥራቅ አልያም በአፍሪካ ከሆነ ደግሞ ለእንደዚህ አይነት ጥቃቶች ይበልጥ ተጋላጭ ነዎት ይላል።

መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

ደግነቱ እንዲህ አይነቱን ጥቃት በቀላሉ መከላከል እንችላለን። የመጀመሪያው ምክር የሚሆነው የራስዎትን ገመድ መጠቀም ነው።

ሌሎች አማራጭ መከላከያዎች፡

• ከቤትዎ ሲወጡ ስልክዎትን በደንብ ቻርጅ ማድረግ

• ተጨማሪ ቻርጅ ማድረጊያ (ፓወር ባንክ) ይዞ መንቀሳቀስ

• የተለያዩ መከላከያዎችን በስልክዎት ላይ መጫን

መርሳት የሌለብን ግን ለስለላ አገልግሎት የሚውሉ ሶፍትዌሮች በስልኮቻችን ላይ ከምንጭናቸው መተግበሪያዎች ጋር ተለጥፈውም ሊገቡ እንደሚችሉ ነው።

ሌላኛው ደግሞ በየትኛውም ምክንያት ይሁን የስለላ ሶፍትዌሮቹ ወደ ስልካችን ከገቡ በኋላ ከዚህ በፊት አይተናቸው የማናውቃቸው ማስታወቂያዎችን ይዘው ይመጣሉ።

ብዙዎች ደግሞ ዘግቶ ከማለፍ ይልቅ ማስታወቂያዎቹን ከፍተው ለመመልከት ይሞክራሉ። ይህ ደግሞ አሁንም ለተለያዩ ጠላፊዎችና በርባሪዎች ያጋልጠናል።

ሌሎች ደግሞ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት መልክ ሊመጡ ይችላሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ