የማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች እያበቃላቸው ነው?

ሴት ተማሪ በክፍል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እየኖርንበት ባለነው ዘመናዊው ዓለም ሥራ ለማግኘት ቢያንስ ዲግሪ መያዝ አስፈላጊ እየሆነ የመጣ ይመስላል። ነገር ግን ዲግሪ ብቻውን ሥራ ለማግኘት በቂ ያማይሆንባቸው ሁኔታዎችም እየተፈጠሩ ነው።

አሜሪካ ውስጥ በግል ዩኒቨርሲቲ ተምሮ ለመጨረስ በዓመት ቢያንስ እስከ 49 ሺህ ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ በእንግሊዝ ደግሞ ከዚህ ዝቅ ብሎ 12 ሺህ ዶላር አካባቢ ነው። በእስያዋ ሲንጋፖር ደግሞ በአንድ የግል ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመት ለመማር 51 ሺህ ዶላር ሊያስወጣ ይችላል።

ለእውቀት ብቻ ብሎ መማር እጅግ የሚበረታታ ነገር ቢሆንም ብዙ ገንዘብ አውጥተን የተማርነው ትምህርት መልሶ እንዲከፍለን እንፈልጋለን።

ለምሳሌ አንድ የዲግሪ ባለቤት አሜሪካዊ ዲግሪ ከሌለው አንድ ሰው በተሻለ በሳምንት ተጨማሪ 461 ዶላር ያገኛል።

እዚህ ጋር ተያይዞ አብሮ የሚነሳው ደግሞ የተሻለ ገንዘብ ማስገኘት የሚችሉ የትምህርት አይነቶች ተብለው የሚመረጡ መኖራቸውን ነው። ብዙውን ጊዜ ጥሩ ገንዘብ ማግኘት የሚፈልግ ሰው 'ስቴም' ተብለው የሚታወቁትን ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ እንዲማር ይነገረዋል።

ይሄ ማለት ግን ማኅበራዊ ሳይንስ፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና እና ቋንቋዎችን የመሳሰሉ የትምህርቶች አይነቶች ተፈላጊ አይደሉም ማለት ነው?

የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች ዋነኛ ትኩረታቸው ተማሪዎች በጥልቀት እንዲያስቡ፣ እንዲተቹና ሃሳባቸውን በትክክል መግለጽ እንዲችሉ ማድረግ ነው። ነገር ግን በቴክኖሎጂ እየተናጠች የምትገኘው ዓለማችን ለማህበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች አስቸጋሪ እየሆነች ይመስላል።

የቴክኖሎጂውን ዘርፍ በመሪነት ከተቆጣጠሩት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቻይና እንኳን ካሏት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል 42ቱን በዓለም ምርጥ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ለማድረግ እየሰራች ነው።

የእንግሊዝ መንግሥት ደግሞ ትኩረቴን ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አድርጌያለው ካለ በኋላ ማኅበራዊ ሳይንስን የሚቀላቀሉ የአገሬው ተማሪዎች ቁጥር 20 በመቶ መቀነሱ ታውቋል።

የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች እንደሚሉት ለእነዚህ ትምህርቶች ትኩረት መንፈግ ማለት እራሳችንንና በዙሪያችን ያለውን ዓለም ለመረዳትና ለማሻሻል ያለንን እድል አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል።

የግለሰብና ማኅበራዊ ደህንነት፣ ፈጠራን ማበረታታት፣ መቻቻል እንዲኖር መስራት፣ ሕግና ደንብ ማዘጋጀት፣ ባህልና ታሪክን ማሳደግ እንዲሁም ህጻናትን አንጾ ማሳደግን የመሳሰሉ ነገሮች ያለማኅበራዊ ሳይንስ የማይታሰብ ነው።

ጆርጅ አንደርስ ለፎርብስ መጽሄት ይዘግብ የነበረ ጋዜጠኛ ነው። ''ከ2012 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት የቴክኖሎጂ ሪፖርተር ነበርኩኝ። ባሳለፍኳቸው ዓመታት ሰዎች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጪ ትምህርት ያለ አይመስላቸው ነበር'' ይላል።

''ሃሳብን በቀላሉ መግለጽ መቻል፣ ከሰዎች ጋር ተስማምቶ መኖር፣ የሌሎች ሰዎችን ሀሳብ መረዳት፣ ረቂቅ ሀሳቦችን በቀላሉ ለሰዎች ማስረዳት መቻልና የመሳሰሉ ችሎታዎች የትኛውንም የሥራ አካባቢ የተሻለ ያደርጋሉ። እነዚህ ደግሞ ያለ ማኅበራዊ ሳይንስ የሚታሰቡ አደሉም።''

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከ22 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ያቀፈው ታዋቂው የታክሲ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ኡበር እንኳን ይህንን በመረዳት ይመስላል በማኅበራዊ ሳይንስ በተለይ ደግሞ በሥነ ልቦና (ሳይኮሎጂ) ዲግሪ ያላቸውን ሰዎች እንደሚመርጥ አስታውቋል።

'ሊንክድኢን' የተባለው የሥራ ማፈላለጊያ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ 2019 ዓ.ም ቀጣሪዎች ይፈልጓቸዋል ያላቸውን ችሎታዎች ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት ነገሮችን በሌላ ዕይታ መመልከት የሚችል፣ ሰዎችን ማሳመን የሚችል፣ በቡድን መስራት የሚችልና ከፍ ሲል ደግሞ ብዙ ሠራተኞችን ማስተዳደር የሚሉት በብዛት ይጠቀሳሉ።

በእንግሊዝ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት ደግሞ 56 በመቶ የሚሆኑት የእንግሊዝ ቀጣሪዎች ካሏቸው ሠራተኞች መካከል 46 በመቶዎቹ እርስ በእርሳቸው መግባባት የማይችሉና ሃሳባቸውን እንኳን በአግባቡ መግለጽ የማይችሉ ናቸው።

የአሜሪካው ትልቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አምራች ኩባንያ ማይክሮሶፍት በበኩሉ የምንፈጥራቸው ኮምፒዩተሮች በቅርብ ዓመታት ውስጥ ልክ እንደ ሰው ልጅ መሆን መጀመራቸው ስለማይቀር የማኅበራዊ ሳይንስ ምሩቃን ተፈላጊ ይሆናሉ ብሏል።

እነዚህን ሰው መሰል ኮምፒዩተሮች የሰው ልጅን ገጽታና አስተሳሰብ ለማላበስ ቋንቋ፣ እደጥበብና ሥነ ጥበብ፣ ታሪክ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ሥነ ምግባር፣ ማኅበራዊ ሳይንስ፣ ፍልስፍና እንዲሁም ሥነ ልቦና ማስተማር ያስፈልጋል።

ያለማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ደግሞ ይህ አይሆንም፤ ስለዚህ የወደፊቱ የሰው ልጅ ተስፋ በማኅበራዊ ሳይንስ ምሩቃን ላይ ሊሆን እንደሚችል ማይክሮሶፍት ገልጿል።

የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው እንዲከራከሩ፣ መጽሐፍትን አንብበው ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ፣ ግጥም እንዲጽፉ፣ ስዕል እንዲስሉና የታዋቂ ምሁራንን ምርምሮች እንዲተቹ ይደረጋሉ። ይህ ደግሞ ምን አይነት ጥቅም እንዳለው ማንም ይረዳዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ከሌሎች ተማሪዎች በተለየ አንድን ግለሰብም ሆነ ማኅበረሰብን በቀላሉ መረዳትና መርዳት ይችላሉ።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ምሩቁ ሊስትሮ

በማኅበራዊ ሳይንስ ከሚመረቁ የአሜሪካ ተማሪዎች መካከል 15 በመቶ የሚሆኑት በተለያዩ ድርጅቶች በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚያገኙ ሲሆን 14 በመቶዎቹ ደግሞ በቢሮ አስተዳደር ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።

ቀሪዎቹ ደግሞ በሽያጭና አስተማሪነት ዘርፎች እንደሚሰማሩ አንድ መረጃ ይጠቁማል።

በርካታ በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች የሚመረቁ ተማሪዎች እንደ የህክምና ዶክተሮች አልያም እንደ መሐንዲሶች ሁሉ ጥሩ ገቢን የሚያስገኝ ሥራ እንደማያገኙ ያስባሉ።

በ30 የተለያዩ የዓለማችን አገራት በሚገኙ 1700 ሰዎች ላይ በተደረገ አነስተኛ ጥናት መሰረት ግን፤ በከፍተኛ ኃላፊነትና ሠራተኞችን በማስተዳደር ላይ ከተሰማሩት መካከል 80 ከመቶ በላይ የሚሆኑት በማኅበራዊ ሳይንስ ዲግሪ አላቸው።

በተለይ ደግሞ በእድሜ ትንንሾቹ ኃላፊዎች አብዛኛዎቹ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሩቃን ሲሆኑ እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑት ግን 'ስቴም' የሚባሉትን ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድንና እና ሒሳብ የተማሩ ናቸው።

የትምህርት ባለሙያዋ ሜገን ቲርስ ግን "ተማሪዎች ሁሌም ቢሆን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ሲገቡ ማሰብ ያለባቸው ስለ ጥሩ ደሞዝ አልያም ሊያስገኝላቸው ስለሚችለው የሥራ ዕድል ሳይሆን ዘርፉ ምን ያህል ደስተኛ ያደርገኛል የሚለውን መሆን አለበት" ትላለች።

ምናልባት ቤተሰቦችና ጓደኞች ይህንን ምረጡ ይህን አስቀድሙ ሊሉ ይችላሉ፤ ዋናው ቁምነገሩ ግን የሚወዱትንና ውጤታማ መሆን የሚችሉበትን ዘርፍ በጥንቃቄ ለይቶ ማወቅ እንደሆነ ትገልጻለች።