አቶ ለማ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር መስማማታቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, EPRDF official
"ልዩነቱ የግል ሀሳብን በነፃነት ማራመድን የሚያመላክት ዴሞክራሲያዊ መብት የተንፀባረቀበት እንጂ የተካረረ የግለሰቦች ፀብ አልነበረም"
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በገዢው ፓርቲ ውህደትና እየተከተለ ባለው አካሄድ ላይ እንደማይስማሙ በመግለጽ ልዩነታቸውን አሳውቀው የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ከአዲሱ ፓርቲ ጋር አብረው ለውጡን እንደሚያስቀጥሉ ተነገረ።
የኢህአዴግ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የሰፈረው መልዕክት፣ በመከላከያ ሚኒስትሩ በአቶ ለማና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መካከል ጉልህ ልዩነት እንደተፈጠረ ተደርጎ የተነገረው ትክክል አለመሆኑን ጠቅሷል።
አክሎም "ልዩነቱ የግል ሀሳብን በነፃነት ማራመድን የሚያመላክት ዴሞክራሲያዊ መብት የተንፀባረቀበት እንጂ የተካረረ የግለሰቦች ፀብ አልነበረም" በማለት የተከሰተው ለውጡ ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ በሚመራበት መንገድ ላይ የተወሰነ "የአካሄድ ልዩነት" እንጂ ሲነገር እንደነበረው የጎላ አልነበረም ብሏል።
ይህንን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ኢንጂነር ታከለ ኡማ በትዊተር ገጻቸው ላይ አጭር መልዕክት አስፍረው የነበረ ሲሆን ትናንት አመሻሽ ላይም የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ዝርዝር የሌለው አጭር ዜና አውጥቶ ነበረ።
ሁለቱ ከፍተኛ የመንግሥትና ፓርቲው አመራሮች በተፈጠረው ልዩነት ላይ ቁጭ ብለው መወያየታቸውንና ተፈጥሮ የነበረውን የሐሳብ ልዩነት ላይ መግባባት እንደቻሉና አብረው ለመስራት መስማማታቸው ተገልጿል።
በዚህም ሁለቱ መሪዎች የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በጋራ በመስራት እውን ለማድረግ ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን ፓርቲው በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስፍሯል።
የመደመር እሳቤን መሰረት አድርጎ ከህወሓት በስተቀር ቀሪዎቹን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችንና አጋር የተባሉትን ፓርቲዎች በማቀፍ የተመሰረተውን የብልጽግና ፓርቲ ይፋ መሆን ተከትሎ አቶ ለማ መገርሳ ልዩነት እንዳላቸው በተናገሩበት ጊዜ ግራ መጋባት ተፈጥሮ ነበር።
አቶ ለማ በፓርቲዎቹ ውህደት ላይ ያላቸውን ጥያቄና የተሄደበት መንገድን በማንሳት የተለየ አቋም ከማንጸባረቃቸው ባሻገር ተሰሚነት እንዳልነበራቸው ጠቅሰው ነበር።
ይህንን ተከትሎም ከተለያዩ ወገኖች በፓርቲው ውስጥ ስለሚኖራቸው ቀጣይ ዕጣ ፈንታና ይህ ልዩነትም የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ መላምቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።
አሁን ከፓርቲው በኩል የሚወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ለማ በልዩነታቸው ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተው መግባባት ላይ እንደደረሱና የተጀመረውን ለውጥ በጋራ ለማስቀጠል እንደተስማሙ ተገልጿል።