ከጀማል ኻሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ አምስት ሰዎች ሞት ተፈረደባቸው

ጋዜጠኛ ከማል ኻሾግጂ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ባለፈው ዓመት ከተገደለው ጋዜጠኛ ከማል ኻሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ የሳኡዲ አረቢያ ፍርድ ቤት አምስት ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ መወሰኑን የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ።

የሳኡዲ መንግሥት ዋነኛ ተቺ እንደሆነ የሚነገርለት ኻሾግጂ ቱርክ ኢስታምቡል ውስጥ በሚገኘው የሳኡዲ አረቢያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ ነበር በደህንነት ሰራተኞች የተገደለው።

የሳኡዲ መንግሥት ዐቃቤ ሕግ "ጭካኔ የተሞላበት ተግባር" ያለውን ግድያ ተከትሎም ስማቸው ያልተጠቀሱ አስራ አንድ ሰዎችን ለፍርድ አቅርቧል።

በጀማል ኻሾግጂ ላይ የተፈጸመው ግድያ በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያ ከመሆኑ ባሻገር በሳኡዲ መንግሥት ላይ ከባድ ውግዘትን አስከትሎ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ግድያውን "ከሕግ ውጪ የተፈጸመ ግድያ" ሲል አቅግዞታል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ልዩ ተጠሪ የሆኑት አግነስ ካላመርድ ከግድያው ጋር በተያያዘ የሳኡዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ላይ ምርመራ እንዲደረግባቸው ጥሪ አቅርበው ነበር።

ልዑሉ ቀደም ሲል በጋዜጠኛው ግድያ ውስጥ ምንም ተሳትፎ እንደሌላቸው ቢያስተባብሉም፤ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ግን እንደሳኡዲ መሪነታቸው የድርጊቱን ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ተናግረዋል።