ቦይንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚውን አባረረ

የቦይንግ ሥራ አስፈፃሚ ዴኒስ ሚሌንበርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አውሮፕላን አምራቹ ኩባንያ ቦይንግ፤ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴኒስ ሚሌንበርግ ከኃላፊነታቸው አነሳ።

እርሳቸውን ከኃላፊነት የማንሳቱ እንቅስቃሴ የመጣው አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ማምረቱን ለጊዜው ሊያቋርጥ እንደሚችል ከገለፀ በኋላ ነው።

የቦይንግ ምርት የሆኑት ሁለት 737 ማክስ 800 አውሮፕላኖች መከስከሳቸውን ተከትሎ ለዘጠኝ ወራት ያህል ሞዴሉ እገዳ ተጥሎበት ቆይቷል።

የአሁኑ ሊቀመንበር ዴቪድ ካልሆን የዋና ሥራ አስፈፃሚ ኃላፊነቱን እና ፕሬዚደንት ሆነው ከፈረንጆቹ ጥር 13 ጀምሮ ማገልገል ይጀምራሉ።

ላውረንስ ኬልነር ደግሞ የድርጅቱ የቦርድ ኃላፊ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉም አክሏል።

"የዳይሬክተሮች ቦርድ፤ በካምፓኒው ላይ በራስ መተማመንን ለመመለስ፣ ወደፊት ተጠናክሮ ለመቀጠል እንዲሁም ከደንበኞች፣ ተቆጣጣሪዎች እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ያለን ግንኙነት ለማጠናከር፤ አመራር መቀየር አስፈላጊ እንደሆነ ወስኗል" ሲል ቦይንግ በመግለጫው ምክንያቱን አስቀምጧል።

በካምፓኒው አዲስ አመራር ሥር፤ ቦይንግ ከፌደራል አቪየሽን ባለሥልጣን [FAA] እንዲሁም ከተቆጣጣሪዎች እና ደንበኞች ጋር ግልፅ የሆነ፣ ውጤታማና የተቀላጠፈ ኮሚዩኒኬሽን እንዲኖረው የሚያስችል አሰራርም እንደሚያሻሽል አክሏል።

ቦይንግ 737 ማክስ 800 አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰከሰውን አውሮፕላን ጨምሮ ሁለት የከፉ አደጋዎች መድረሳቸው ይታወሳል።

መጋቢት ላይ ኢቲ 302 ቦይንግ 737 ማክስ 800 ሲከሰከስ በአውሮፕላኑን ተሳፍረው የነበሩ 157 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ከኢቲ በፊት የኢንዶኔዥያው ላየን ኤር ተከስክሶ 189 ሰዎች መሞታቸውም አይዘነጋም።

ተሻሻለ የተባለው ሶፍትዌር ምንድነው?

ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም) ለሚለው ምህጻረ ቃል ነው። ይህ ሲስተም አውሮፕላኑን የሞተሩ ክብደትና የተቀመጠበትን ቦታ ምክንያት አድርጎ እንዳይቆምና እንዳያጋድል ያደርገዋል።

ይህም አውሮፕላኑ ሽቅብ በሚወጣ ጊዜ የሚያሳየውን ዝማሜ ተከትሎ ሚዛኑን እንዲያስጠብቀው ለማድረግ የተሠራ ነበር።

ነገር ግን የኢንዶኒዢያው ላየን አውሮፕላን ምርመራ ውጤት እንዳመላከተው ይህ ሴንሰር አውሮፕላኑ በአፍጢሙ እንዲደፋ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚልከው መልዕክት (ሲግናል) እርስበርሱ የሚጣረስ በመሆኑ ነው።

ይህም ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ነገር ነው። የተከሰከሰው የኢንዶኒዢያ አየር መንገድ ከ20 ጊዜ በላይ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል እንዲያዘምና እንዲምዘገዘግ አድርጎታል።

አሁን ቦይንግ አድሼዋለሁ የሚለው ሶፍትዌር በአውሮፕላኑ አፍንጫ የምትገኘው ሴንሰር እርስበርሱ የሚጣረስ ምልእክት ካስተላለፈ ኤምካስ የተሰኘውን መቆጣጠሪያ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ባልቦላ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚያደርግ ነው።