በአሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት 60 መኪኖች በመገጫጨታቸው በሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

ጉዳት የደረሰባቸው መኪኖች ከአደጋው በኋላ

የፎቶው ባለመብት, YORK-POQUOSON SHERIFF'S OFFICE/AFP

በአሜሪካ በአንድ የፍጥነት አውራ ጎዳና ላይ ባጋጠመ አደጋ ከ60 በላይ መኪኖች ሲገጫጩ በ50 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ደረሰ።

በቨርጂኒያ ግዛት ላጋጠመው አደጋ ጭጋጋማ የአየር ንብረት ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።

በትራፊክ አደጋው የሞተ ሰው ባይኖርም ከተጎዱት 50 ሰዎች መካከል ሁለቱ ለሕይወታቸው አስጊ የሆነ ጉዳት እንዳጋጠማቸው ፖሊስ አስታወቋል።

በተሽከርካሪዎች ላይም ከከባድ እስከ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

ከጭጋጋማ የአየር ንብረት በተጨማሪ በመንገዱ ላይ የነበረው በረዶ መኪኖች እየንሸራተቱ ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆኑ እንዳደረገ የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

በአደጋው ሥፍራ የተነሱ ፎቶግራፎች በርካታ መኪኖች እርስ በርስ ተገጫጭተው እና አንዱ በአንዱ ላይ ወጥቶ አስልመልክተዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም ተጎጂዎችን እና መኪኖችን አንስተው መንገዱን ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ ረጅም ሰዓት ወስዶባቸዋል።

የከባድ መኪና አሽከርካሪው ኢቫን ሌቪ ለአሶሲየትድ ፕሬስ ሲናገር፤ "ጭጋጋማ የአየር ንብረት ስለነበረ መኪኖች ከሩቅ እንዲመለከቱኝ የአደጋ ጊዜ መብራት አብርቼ በዝግታ እየሄድኩ ነበር። ከዛ በኋላ የማስታውሰው በጣም ብዙ መኪኖች ተጋጭተው እርስ በራሳቸው ላይ ተደራርበው ነው" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፎቶው ባለመብት, Reuters