የአልኮል ችግር ያለባቸው ወንዶች ጥቃት የመፈጸም እድላቸው ከፍ ያለ ነው

አልኮል የሚጠጣ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty

የአልኮል ወይም የማንኛውም አይነት ሱስ ያለባቸው ወንዶች አጋሮቻቸው ላይ ጥቃት የመፈጸም እድላቸው ሱስ ከሌለባቸው ሰዎች በስድስት ወይም ሰባት እጥፍ ከፍ እንደሚል አንድ ጥናት ጠቆመ።

'ፕሎስ ሜድሲን' የሚባለው የበይነ መረብ ጆርናል ላይ የታተመው ጥናት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጤና መዛግብትንና የ16 ዓመታት የፖሊስ ሪፖርትን እንደ መነሻ አድርጎ ነው የተሰራው።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ሲና ፋዜል ጥናቱን የመሩት ሲሆን ''ባገኘነው ውጤት መሰረት የአልኮልና ሌሎች ሱሶችን መቆጣጠርና ማከም ከቻልን በተለይ በሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መቀነስ እንችላለን'' ብለዋል።

''ሱስ እንዳይከሰት ቀድሞ መከላከል እንዲሁም ከተከሰተ በኋላ በአግባቡ መከታተል የሚችል ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል። ጥቃት ፈጻሚዎችም ሱሰኛ ስለሆኑ ብቻ በቀላሉ መታለፍ የለባቸውም።''

የእንግሊዝ፣ አሜሪካ እና ስዊድን ባለሙያዎችን ያሳተፈው ጥናት ከአውሮፓውያኑ 1998 እስከ 2013 ባሉት ዓመታት የአልኮልና ሌሎች ሱሶች ያሉባቸው 140 ሺ ወንዶችን መረጃ ተጠቅሟል።

በመቀጠልም እነዚህ ሰዎች ምን ያክል ጊዜ ሰዎችን እንዳስፈራሩ፣ ጾታዊም ሆነ ሌላ ጥቃት መፈጸማቸውን እና ምን ያክል ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተመልክቷል።

በዚህ መሰረት በአልኮል የሚጠቁ ወንዶች ሱሱ ከሌለባቸው ጋር ሲነጻጸሩ በፍቅር አጋሮቻቸው ላይ ጥቃት የመፈጸም እድላቸው ከስድስት እስከ ሰባት እጥፍ ከፍ እንደሚል ተመራማሪዎቹ ደርሰንበታል ብለዋል።

የአልኮል ችግር ያለባቸው ወንዶች 2.1 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በፖሊስ ቁጥጥር ውለዋል።

ከዚሁ ጥናት የተገኘው ሌላ ወሳኝ መረጃ ደግሞ የአልኮል ሱሰኛ ወንዶች በፍቅር አጋሮቻቸውም ሆነ ሌሎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት በሰከሩበት ወቅት ብቻ አለመሆኑ ነው።

ባልጠጡበት ወቅት እንኳን በጣም ሰዎችን መቆጣጠር የሚወዱና ቁጡ ናቸው ይላል ጥናቱ።

በሌላ በኩል እንደ ቀላል የሚታዩ የአእምሮ ጤና ችግሮችም ወንዶች ፊታቸውን ወደ አልኮልና ሌሎች ሱስ አስያዥ ንጥረነገሮች እንዲያዞሩ ያደርጋቸዋል።