የኢንዶኔዢያው ባስ ወንዝ ውስጥ ገብቶ ቢያንስ 25 ሰዎች ሞቱ

ፖሊስ በአደጋው ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Palembang Search and Rescue Agency/Instagram

በኢንዶኔዢያ በርካቶችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው የሕዝብ ማማላሻ መኪና መንገዱን ስቶ ቁልቁል ከተወረወረ በኋላ ወንዝ ውስጥ መውደቁን ተከትሎ ቢያንስ 25 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች 13 ደግሞ ጉዳት ደርሰቦቸዋል።

ሾፌሩንና ከ 37 በላይ ተሳፋሪዎችን ይዞ የነበረው ተሽከርካሪ በደቡባዊ ሱማትራ ግዛት ሰኞ ምሽት አደጋው ካጋጠመው በኋላ ቁልቁል 100 ሜትር ያህል ተምዘግዝጓል።

የአገሪቱ ባላሥልጣናትም አደጋውን ተከትሎ የሟቾችን አስክሬን እንዲሰበስቡና በሕይወት ያሉትን እንዲረዱ 120 አባላት ያሉት የፍለጋ ቡድን አሰማርተዋል።

አደጋው በምን ምክንያት እንደተከሰተ ባለማወቁ በምርመራ ላይ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።

ቤንግኩሉ ከምትባለው ከተማ የተነሳው ተሽከርካሪ በጥቂት ሰዓታት ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሱማትራ ደሴት በመሄድ ላይ እንደነበር የአገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

የአካባቢው የፖሊስ ኃላፊ ዶሊ ጉማራ እንዳሉት በሕይወት የተረፉትን የመፈለግ ሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።

''ሥራው ከባድ ቢሆንም በሕይወት ላሉት ቅድሚያ በመስጠት ጀምረናል። የሟቾችንም ሆነ የተረፉት ሰዎች ቤተሰቦች ወደቦታው በመምጣት ማንነታቸውን እንዲለዩ ጥሪም አቅርበናል'' ብለዋል ኃላፊው።