የኢትዮጵያን አፈር ለማከም የሚመራመረው ዶ/ር መሐመድ አባኦሊ

ዶ/ር መሐመድ አባኦሊ

የፎቶው ባለመብት, MOHAMMED ABAOLI

በአሁን ወቅት በአሜሪካ፣ አትላንታ የሚገኘው ዶ/ር መሐመድ አባኦሊ በእጽዋትና በአፈር ላይ ይመራመራል፤ ስለ አየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ስለብዝሀ ሕይወት ጥበቃም ያጠናል።

ዶ/ር መሐመድ በቅርቡ 'ኢንተርናሽናል ኤጀንሲ ፎር ስታንዳርድስ ኤንድ ሬቲንግ' በተባለ ተቋም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2019፣ በባዮማስ ዴንሲቲ የዓለም ተሸላሚ ሆኗል።

ተመራማሪው በዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ ሽልማት ሲያገኝ ይህ ሦስተኛው ነው። በ2019 በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሠራው ሌላ ጥናትም እውቅና ተሰጥቶታል። 'ግሎባል ጆርናል'ን ጨምሮ በተለያዩ የሳይንስ መጽሔቶች በቦርድ አባልነት የሚሠራው ተመራማሪው፤ በባዮማስ ዴንሲቲ ዙርያ የሠራው ጥናት፤ የኢትዮጵያን አፈር ማከም እንዲሁም አርሶ አደሩ ለዘለቄታው ከመሬቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ያመላከተ ነው።

ባዮማስ ዴንሲቲ (እጽዋት በምን ፍጥነትና እንዴት እንደሚያድጉ የሚጠናበት ዘርፍ ነው) ከዶ/ር መሐመድ የምርምር ትኩረቶች አንዱ ነው። ለሽልማት ያበቃው ጥናት፤ እጽዋት ሥራቸው ምን ያህል አፈርን ሸፍኖታል? በሚል በትውልድ ቀዬው በጅማ ዞን በሚገኘው ጊራ የተሠራ ነው።

በአካባቢው ኬሚካል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ በዋለበትና ባልዋለበት መሬት መካከል ያለው የአፈር ምርታማነት ልዩነት ላይ እንዳተኮረ የሚናገረው ዶ/ር መሐመድ እንደሚያስረዳው፤ ኬሚካል ማዳበሪያ አፈር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።

አፈር ውስጥ የሚኖሩ ሕይወት ያላቸውና ለአፈር ጤናማነት እንዲሁም ምርታማነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች በኬሚካል ማዳበሪያ ሳቢያ ጉዳት ይደርስባቸዋል። ጥናቱም በኬሚካል ማዳበሪያ የተበላሸ መሬት እንዴት ማገገም ይችላል? የሚለውን የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያመላክት ነው።

"የኛ ሕዝብ መሬቱን ውጤታማ ለማድረግ ብሎ ኬሚካል ማዳበሪያ ሲጨምር እነዚህ ጠቃሚ ነገሮች ከአፈሩ ይጠፋሉ፤ እነሱ ሲጠፉ ደግሞ ምርታማነት ይቀንሳል፤ እኔ ያጠናሁት በዚህ አይነት የተጎዳ አፈር እንዴት እንዲያገግም ማድረግ ይቻላል? የሚለውን ነው"

የፎቶው ባለመብት, MOHAMMED ABAOLI

አፈር እንዴት ያገግማል?

ዶ/ር መሐመድ ጥናቱን የሠራው በተለያዩ እጽዋት ላይ ሲሆን፤ ምርምሩን ለማገባደድ ወደ አንድ ዓመት ተኩል ወስዶበታል። አንድ ተክል የሆነ አካባቢ ከተተከለ ምን ያህል ወደ ውስጥ ገብቶ ያን አፈር ሊያገግመው ይችላል? ወደ ጎን እስከ ስንት ሜትር ድረስ ሊያገግም ይችላል? በሚለው ተመርኩዞ ያ ተክል እንዲበቅል ይመከራል ወይስ አይመከርም? የሚለውን በጥናቱ መመልከቱን ያስረዳል።

ጥናቱን በሠራበት አካባቢ፤ ቀደም ባለው ጊዜ አርሶ አደሮች ኬሚካል ማዳበሪያ እንደማይጠቀሙ፣ መሬቱም ምርታማ እንደነበር ያስታውሳል። ዩሪያ እና ዳፕ ማዳበሪያ ሲጠቀሙ ግን የአፈር ምርታማነት በጣም እየቀነሰ፣ አንዳንዱ አካባቢ ሳር እንኳን ማብቀል እንዳልቻለም አርሶ አደሮቹ ነግረውታል።

"ኬሚካል ማዳበሪያ በግብርና ምርት ጥቅም እያመጣ ቢሆንም፤ መሬቱ ሁለት ሦስቴ አምርቶ ከዚያ በኋላ እንዲጠፋ ያደርጋል። በእኛ አገር ደግሞ ጥናት ሳይደረግ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተመሳሳይ ዩሪያ እና ዳፕ ለአርሶ አደሩ ስለሚከፋፈል በጣም ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።"

በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ያለው የግብርና መሬት የተለያየ ቢሆንም ለሁሉም በደምሳሳው ተመሳሳይ አይነት የኬሚካል ማዳበርያ ጥቅም ላይ መዋሉ ምርት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ዶ/ር መሐመድ ይገልጻል።

በሌሎች አገሮች በአግባቡ መሬት ተለክቶ፣ በባህሪው መሠረት ቢሠራም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታ ከዚህ በተቃራኒው እንደሆነ ያክላል።

"አርሶ አደሮችን ኬሚካል ማዳበርያ ካልወሰዳችሁ ተብለው ይገደዳሉ። ቢወስዱም ባይወስዱም ገንዘብ ስለሚከፍሉ ወስደው የሚጥሉትም አሉ" የሚለው ተመራማሪው፤ ኬሚካል ማዳበሪያ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከግምት ሳይገባ ንግድ ተኮር ንቅናቄ መደረጉን "አገራዊ ኪሳራ" ሲል ይገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ምን ይጠቀም?

ተመራማሪው ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው መሬት ምን ባህሪ እንዳለው ለማጥናት ነው። ከዚያ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፣ በተጠና መንገድ ኬሚካል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ይውላል እንጂ ለሁሉም አይነት መሬት መዋል የለበትም ይላል።

"ለምሳሌ ደጋ አካባቢ ብንሄድ. . . አብዛኞቹ የአገሪቱ ማዳበሪያዎች ኤንፒኬ (ከናይትሮጅን፣ ፎስፈረስ፣ ፖታሽየም) የተሠሩ ናቸው። ደጋ አካባቢ ደግሞ ናይትሮጅን ሙሉ ነው። አንቺም የምትጨምሪበት ናይትሮጅን ይሆናል። ናይትሮጅን ደግሞ የሚያበዛው ባዮማሱን ነው። (ቅጠል እና ግንድ ነው የሚያበዛው) ግንዱ የማይበላበት አካባቢ ከሆነ ፍሬ አይሰጥም። እንዲያውም ቶክሲክ [መርዛማ] እየሆነበት ይሄዳል።"

ዶ/ር መሐመድ ይህን ምሳሌ ማሳያ አድርጎ፤ ምርታማንትን ለማሳደግ የመሬት አይነትን ማወቅ፣ ከዚያም ኬሚካል ያስፈልጋል? የሚለውን መገንዘብ የግድ ነው ይላል።

አፈር እንዲያገግምና የመሬት ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ ሌላው አማራጭ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን መጠቀም ነው። ለምሳሌ እህል ከተሰበሰበ በኋላ ገለባውን ከመጣል፣ መልሶ ለማዳበሪያነት መጠቀም ይቻላል።

አርሶ አደሩ ለምን ኬሚካል ማዳበሪያ እንዲጠቀም ይገደዳል?

ዶ/ር መሐመድ አርሶ አደሮች የኬሚካል ማዳበሪያ ለመጠቀም የሚገደዱት ማዳበሪያውን ከመሸጥ የሚገኘው ትርፍ ብቻ ስለሚታሰብ መሆኑን ያስረዳል።

"የግብርና ፖሊሲው መሬት ተኮር ሳይሆን ሰው ተኮር ነው፤ የሚታሰበው ስለ አገር ሳይሆን አሁን ላይ ተሽጦ ስለሚገኘው ገንዘብ ብቻ ነው።"

የኬሚካል ማዳበሪያ ሲገዛ አምራቹን አገር ለመጥቀም የሚታሰበውን ያህል ቀጣይነት ስላለው ምርት አለመወጠኑን ይተቻል። ለየትኛው አካባቢ ያስፈልጋል? የተጎዳው መሬት የትኛው ነው? የሚለው ተጠንቶና አርሶ አደሩ ከግምት ገብቶ መካሄድ እንዳለበትም ይመክራል።

"መሬት ከትውልድ ወደ ትውልድ ምርታማነቱን ይዞ መሸጋገር አለበት። መሬት ላይ መጋደል ሳይሆን መሬቱን አለመግደል የተሻለ ነው። የእከሌ መሬት. . . የእኔ፣ ያንቺ እየተባለ ሰው ይጋደላል። መሬቱንም እየገደልን እርስ በእርስም እየተጋደልን ነው። ይህንን ያመጣው ደግሞ የአገሪቱ ፖሊሲ ነው።"

ፈተና የበዛበት ዘርፍ

ኬሚካል ማዳበሪያ የግብርናውን ዘርፍ ከሚፈትኑ አንዱ ቢሆንም ብቸኛው ችግር ግን አይደለም። አብዛኛው ማኅበረሰብ በግብርና በሚተዳደርበት አገር ግብርናው አለመዘመኑ፣ የምርትን ቀጣይነት ማረጋገጥ አለመቻሉም ይነገራል።

ለዶ/ር መሐመድ ቀዳሚው ችግር ሠሪና መሠራት ያለበት አለመገናኘታቸው ነው። በግብርና ዘርፍ ቁልፍ ቦታ የሚሰጣቸው ግብርና ያጠኑ፣ በዘርፉ ልምድ ያካበቱ አለመሆናቸው ዋነኛው ችግር ሆኖ ይታየዋል።

"መሬቱ ምን እንደሚፈልግ፣ አርሶ አደሩ ምን እንደሚፈልግም አይታወቅም፤ እኛ አገር የራሳቸው ፖለቲካ እንዴት ይዘው መሄድ እንዳለባቸው የሚያዩ እንጂ መሬት ላይ ምን እየተከናወነ እንደሆነ አያውቁም።"

ሌላው ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ አለመጠቀም ነው። ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ ካለው ሕዝብ ወደ አንድ በመቶው ብቻ ግብርና ላይ ቢሰማራም፤ ከበቂ በላይ አምርተው ከአገራቸው አልፈው ለሌላ አገርም ይተርፋሉ። አገራቸውን በምጣኔ ኃብት ጠቅመው ለሌላ አገር እርዳታም ይሰጣሉ።

በተቃራኒው ከ80 በመቶ በላይ ዜጋ በግብርና በተሰማራባት ኢትዮጵያ፤ አርሶ አደሩ ራሱን መመገብ ሳይችል በድጎማ ቀለብ ሲኖር ይታያል። ይህን ችግር ለመቅረፍም ቴክኖሎጂን ከግብርና ማስታረቅ የግድ እንደሆነ ተመራማሪው ያምናል።

በሌላ በኩል የግብርና ምርምር ተቋሞች በሚያስፈልገው መጠን፣ ሙከራ [ሳምፕል] ሠርተው ለአርሶ አደሩ የሚጠቅመውን ዘርፍ ማመላከት አለመቻላቸውን ያነሳል።

"እኔ በማውቀው በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ጅማ ውስጥ ያለ የምርምር ማዕከል ከድሮም ጀምሮ ቡና እና አቮካዶ ላይ ብቻ ይሠራሉ። ነገር ግን ግብ ተቀምጦ ሌላ ነገርም መሠራት አለበት።"

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰው ኃይል (አብዛኛው ወጣት)፣ የጊዜ እና የተፈጥሮ ኃብት (መሬትና ብዙ አይነት ምርት ማፍራት የሚቻልበት መልከዓ ምድር) ውጤታማ ሊሆን የሚችለው፤ መንግሥት ምቹ ሁኔታ ሲፈጥር ቢሆንም የግብርና ፖሊሲው ማነቆ መሆኑን ይጠቅሳል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ሮቦት ገበሬዎች የሰዎችን ስራ ሊነጥቁ ነው።

"ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ብቻ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ሕዝቡ ላይ የሚጮህ መንግሥት ሳይሆን፤ አገሪቱን መለወጥ የሚችል ፖሊሲ ለሕዝቡ አቅርቦ ወደ ሥራ መገባት አለበት። አቅጣጫ ሊኖረንም ይገባል።"

በግብርና ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መስኮች ጥናትና ምርምሮች ቢካሄዱም ከመደርደሪያ አልፈው፣ ምክረ ሀሳቦቻቸው እንደማይተገበሩ የሚተቹ ባለሙያዎች አሉ። ግብርናን ስለማሻሻል፣ ቀጣይነት ስላለው ምርታማነት የሚሠሩ ጥናቶች ምን ያህል ተግባራዊ ይደረጋሉ? የሚለው ላይም ጥያቄ ይነሳል።

ስለ አፈር ለምነት፣ ስለ ኬሚካል ማዳበረያ አሉታዊ ተጽዕኖም በተደጋጋሚ በተለያዩ ባለሙያዎች ቢነገርም፤ ጥናቶቻቸውን በመጠቀም ችግሩን ምን ያህል መቅረፍ ተችሏል? የሚለውን ዶ/ር መሐመድን ጠይቀን ነበር።

እሱ እንደሚለው፤ መንግሥት ፖሊሲ ሲረቀቅ እንደ ግብዓት የሚሆኑና የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያመላክቱ ጥናቶችን ለመተግበር ዝግጁ መሆን አለበት። አርሶ አደሩ በኬሚካል ማዳበሪያ ሳቢያ የገጠመው ችግር ለመፍትሔ ሀሳቦች ዝግጁ ቢያደርገውም፤ መንግሥት መፍትሔዎቹን በፖሊሲው ካላካተተ ውጤታማ መሆን አይቻልም።

"ባለሙያዎችን እና ተመራማሪዎችን መጋበዝ፣ ማማከር ያስፈልጋል። በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ቢወጣ ለአገርም ይጠቅማል" ሲል ዶ/ር መሐመድ ሀሳቡን ያስቀምጣል።