ፈረንሳይ ኩሽና ውስጥ ተሰቅሎ የተገኘው ሥዕል ብሔራዊ ሐብት ነው አለች

ሥዕሉ ለበርካታ ዓመታት በኩሽና ውስጥ ከማብሰያ ምድጃ በላይ ግድግዳ ላይ ተንጠልጥሎ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ሥዕሉ ለበርካታ ዓመታት በኩሽና ውስጥ ከማብሰያ ምድጃ በላይ ግድግዳ ላይ ተንጠልጥሎ ቆይቷል።

በአንዲት ፈረንሳዊት አዛውንት ኩሽና ውስጥ የተገኘው ጥንታዊ ስዕል የሥነጥበብ ባለሙያዎችን ሲያስደንቅ ቆይቶ አሁን ላይ የፈረንሳይ መንግሥት ብሔራዊ ቅርስ ነው በማለት ወደ ሌላ ሃገር እንዳይላክ እገዳ ጥሏል።

በእውቅ ጣሊያናዊ ሰዓሊ ተስሎ የነበረው እና ለረዥም ዓመታት ጠፍቶ የቆየው ይህ ሥዕል በአንዲት አዛውንት ፈረንሳዊት ሴት ኩሽና ውስጥ ከተገኘ በኋላ ሪከርድ በሆነ በ24 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ በጨረታ መሸጡ ይታወሳል።

ይህ የሥዕል ሥራ ከሁለት ወራት በፊት ነበር በሰሜናዊ ፈረንሳይ ነበር የተገኘው።

24 ሚሊዮን ዩሮ ከፍሎ የገዛው አካል ማን እንደሆነ በአጫራቾቹ በይፋ ባይነገርም፤ የፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን ግን ሥዕሉን የገዙት የጣሊያን የጥንት የሥዕል ሥራዎችን በመሰበሰብ የሚታወቁ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆኑ ሁለት የቺሊ ዜጎች መሆናቸውን ዘግበዋል።

የፈረንሳይ መንግሥት ይህን የሥዕል ሥራ መልሶ ከግለሰቦች እጅ ለመግዛት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ምንጭ እስኪያገኝ ድረስ ለ30 ወራት ሥዕሉ ከሃገር እንዳይወጣ ወስኗል።

ሥዕሉ ለበርካታ ዓመታት በኩሽና ውስጥ ከማብሰያ ምድጃ በላይ ግድግዳ ላይ ተንጠልጥሎ ቆይቷል። አንድ የሥዕል ባለሙያ እና አጫራች ሥዕሉን ከተመለከተ በኋላ ባለቤቶቹ የሥዕሉን ዋጋ ለማስተመን ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ ሲወተውት ነበር ተብሏል።

ባለቤቶቹ ግን ሥዕሉ እድሜ ጠገብ ሃይማኖታዊ ምልክት ያለው ሥዕል ከመሆን ባለፈ ብዙ ዋጋ ያለው የጥበብ ሥራ መስሎ አልታያቸውም።

በሥዕሉ ላይ የተደረጉ ጥልቅ ምርምሮች ሥዕሉ የጣሊያናዊው ሰዓሊ ሶኒ ዲ ፔፖ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በጣሊያን ፍሎረንስ የተወለደው ሶኒ ዲ ፔፖ በ13ኛው ክፈለ ዘመን መጨረሻ ላይ እና በ14ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሥዕል ሥራዎችን ሰርቷል።

ይህ የጥበብ ሥራ በመጠን አነስተኛ ሲሆን 20 ሲ.ሜትር በ26 ሴንቲ ሜትር ያክላል። ሥዕሉ የአንድ የሥዕል ሥራ አካል ሲሆን የተቀሩት ሥዕሎች ሎንደን እና ኒው ዮርክ በሚገኙ የሥዕል ማሳያ ማዕከል ውስጥ ይገኛሉ።