አቶ ለማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጎልተው የወጡባቸው አጋጣሚዎች

ለማ መገርሳ

የፎቶው ባለመብት, ZACHARIAS ABUBEKER

'ዘ ኢኮኖሚስት' የተሰኘው መጽሄት በ2018 በኢትዮጵያ ''እጅግት ታዋቂው ፖለቲከኛ'' ሲል ለማ መገርሳን መርጦ ነበር። ዛሬም የቀድሞ የጨፌ አፈ-ጉባኤና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት የአሁኑ የመከላከያ ሚንስትሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጽህኖ ፈጣሪነታቸው እንደጎላ እና መነጋገሪያ እንደሆኑ ነው።

ከሦስት ሳምንታት በፊት አቶ ለማ መገርሳ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የኢህአዴግ መዋሃድ እና ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የመደመር ፍልስፍና ጋር እንደማይስማሙ መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እና አቶ ለማ መገርሳ በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚያደርጉት ንግግር እና አንዱ ለአንዱ የሚያሳዩት ተግባራት ሁለቱ ፖለቲከኞች ከትግል አጋርነታቸው በላይ የእርስ በእርስ ቅርርባቸው ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር።

ታዲያ አቶ ለማ በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው በጠቅላይ ሚንስትሩ የመደመር ፍልስፍና እንደማይስማሙ ሲናገሩ በተለይ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ድንጋጤን የፈጠረ ክስተት ነበር።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ከፍተኛ የፓርቲ አባላቶቻቸው አቶ ለማ ያላቸውን የሃሳብ ልዩነት በማጥበብ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር አብሮ ለመስራት መግባባታቸውን ተናግረዋል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው የማይካደው አቶ ለማ፤ ከፍ ሲልም "ለመውደቅና ለመበታተን ከጫፍ ደርሳ የነበረችውን ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንድትቀጥል ያደረጉ ሰው ናቸው" ተብለው እስከ መወደስ ይደርሳሉ።

ለመሆኑ ትውልድ እና እድገታቸው ምሥራቅ ወለጋ የሆኑት የ44 ዓመቱ አቶ ለማ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጎልተው እንዲወጡ ያስቻሏቸው አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?

"ማስተር ፕላን"

2008 ዓ.ም የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተሰኘውን እቅድ በመቃወም በኦሮሚያ ሕዝባዊ ተቃውሞ የተቀጣጠለበት ዓመት ነበር።

ታዲያ የሕዝቡን ተቃውሞ ለማርገብ ከፍተኛ የክልሉ መንግሥት ባለስልጣናት ወደተለያዩ ስፍራዎች በመጓዝ ሕዝቡን የማወያየት ሥራዎችን ሲያከናውኑ ነበር።

በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ወይም ጨፌ አፈ-ጉባኤ የነበሩት አቶ ለማም ወደ ቡራዩ ከተማ በመጓዝ ከከተማው እና ከአካባቢዋ ከተወጣጡ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድረገዋል።

በውይይታቸው ወቅት ማስተር ፕላኑ ሕዝብ የማይፈልገው ከሆነ ሊቀር የሚችል እቅድ ስለመሆኑ ተናግረው ነበር።

የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ማስተር ፕላኑ መተግበሩ እንደማይቀር በሚናገሩበት ወቅት፤ የክልሉ ባለስልጣናት ማስተር ፕላኑን ለሕዝብ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በማስረዳት በተወጠሩበት በዚያን ጊዜ ነበር አቶ ለማ "ማስተር ፕላኑ ሕዝብ ካልፈለገው ይቀራል፤ ከሰማይ የሚወርድ ነገር የለም" የሚል ይዘት ያለው ንግግር ያደረጉት።

የፎቶው ባለመብት, Addisu Arega Kitessa/Facebook

የምስሉ መግለጫ,

በኦሮሚያ "የኢኮኖሚ አብዮት" የሚል እንቅስቃሴ በስፋት አስጀምረው ነበር።

ጥር 2008 ላይ የቀድሞ ኦህዴድ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሙሉ በሙሉ ኦሮሚያ ላይ ተግባራዊ እንደማይደረግ ወሰነ። ከዚያም አቶ ለማ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ።

የለማ ቡድን "ቲም ለማ"

አቶ ለማ የኦህዴድ ሊቀ መንበር እና የክልሉ ፕሬዝደንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ እርሳቸው የመረጧቸውን አባላት በመመልመል 'ቲም ለማ' የተሰኘ ቡድን እንዳቋቋሙ ይነገራል።

ይህ ቡድን ሕዝቡ በወቅቱ ያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን የክልሉ መንግሥት ጥያቄ በማድረግ ምላሸ ለመስጠት ጥረት ያደርግ ነበረ።

በዚያን ወቅትም የክልሉ ገዢ ፓርቲ ኦህዴድ በታሪኩ 'ኦሮምኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን እታገላለሁ" ያለው።

ተከትሎም በሺህዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ከእስር መልቀቁ ፓርቲው በኦሮሚያ ያለው ድጋፍ እንዲጨምር አድርጎለት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Addisu Arega Kitessa/Facebook

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በ'ቲም ለማ' ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክቱ ነበር

ለውጡ በተቃረበበት ጊዜ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ድንበር አቅራቢያ ላይ ተከስቶ የነበረው ግጭት በኦህዴድ ላይ ከፍተኛ ጫና ከፈጠሩ ክስተቶች መካከል የሚጠቀስ ነው።

በዚህም በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በጨለንቆ አካባቢ 16 ሰዎች መገደላቸውን በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ወጥተው መቃወማቸው ከፍተኛ ድጋፍን አስገኝቶላቸዋል።

አቶ ለማ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ከክልሉ እውቅና ውጪ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመግባት በንጹሃን ላያ አድርሷል የተባለውን ጥቃትና ግድያን በግልጽ ነቅፈው ነበር።

'ጌታችን ዝባችን'

ጥር 4/2008 የኦህዴድ 27ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓልን በማስመልከት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ አቶ ለማ ለፓርቲያቸው አባላት ". . . ጌታችን ሕዝባችን ነው። የክልላችን ሕዝብ ነው። ለሌላ ጌታ መስገድ የለብንም" በማለት ተናግረው ነበር።

ይህ የአቶ ለማ ንግግር ህውሓት በኦህዴድ ላይ የነበረውን የበላይነት የሰበረ ነው በማለት አንዳንድ ድርጅቱንና የአገሪቱን ፖለቲካ በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ።

ዶ/ር ሄኖክ ገቢሳ "ህዝብ ተስፋ ቆርጦበት የነበረው ኦህዴድ ተስፋ እንዲዘራበት ያደረገ ንግግር ነው" ሲሉ ያክላሉ።

"ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው"

ከለውጡ ማግስት ጀምሮና በተከታይ በነበሩት ጊዜያት አቶ ለማ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙበት ወቅት ነበር።

ከዚህ ቀጥሎ ያደረጉት ንግግር ከክልላቸው አልፎ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የመንግሥት ባለስልጣናትን፣ አባ ገዳዎችን፣ አርቲስቶችን እና ታዋቂ ግለሰቦችን ይዘው ወደ ባህር ዳር አቀኑ።

የፎቶው ባለመብት, Addisu Arega Kitessa/Facebook

ይህ የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ባለመው መድረክ ላይ "ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው" በማለት ያደረጉት ንግግር በበርካቶች ተወዳጅነትን አስገኘቶላቸዋል።

በወቅቱ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ባስገቡበበት ወቅት፤ ተሰናባቹን ጠቅላይ ሚንስትር ሊተኩ ይችላሉ ተብለው በስፋት ስማቸው ሲነሱ ከነበሩት መካከል አቶ ለማ መገርሳ አንዱ ነበሩ።

ሸገር ታይምስ የተሰኘው መጽሄት በአንድ ዕትሙ አቶ ለማ ኢትዮጵያን በችግር ግዜ ሊያሻግሯት የሚችሉት "ሙሴ" ሲል በፊት ገጹ ላይ ይዟቸው ወጥቶም ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Sheger Times

ስልጣን አሳልፎ መስጠት

ጥር 2010 ዓ.ም ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብዙ ያልተለመደ ክስተት በኦህዴድ ውስጥ ተፈጸሟል። ነገሮች ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆኑና አገሪቱም ወደ አሳሳቢ አቅጣጫ እያመራች መሆኑን ተገነዘቡት የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥራ መልቀቂያ አስገቡ።

ይህንንም ተከትሎ ምንም እንኳን የፌደራሉ ምክር ቤት አባል ባይሆኑም ብዙዎች አቶ ለማ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ ሊይዙ ይችላሉ ብለው ግምት ሰጥተው ነበር።

ነገር ግን የፌደራሉ ፓርላማ አባልና የፓርቲያቸው ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ዐብይ ወደፊት እንዲመጡ መንገድ ለማመቻቸት ሲሉ የኦህዴድ ሊቀ መንበርነት ቦታቸውን እንዲይዙ ማድረጋቸው በርካቶችን አስደንቋል።

ይህም ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ቦታን እንዲይዙና በተለመደው አሰራራም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆኑ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ይስማሙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Addisu Arega Kitessa/Facebook

ወደ መድረኩ መመለስ

አቶ ለማ በመላው አገሪቱ ትኩረትን ያገኙ ፖለቲከኛ መሆን በመቻላቸው ተግባራቸውን ንግግራቸውን በርካቶች በቅርበት ይከታተኩት ነበር። በዚህም በሌሎች ሰዎች ጥቆማ በየዓመቱ በጎ ሥራ ለፈጸሙ የሚሰጠው "የበጎ ሰው ሽልማት" ለአቶ ለማ በ2010 ዓ.ም ተበርክቶላቸዋል።

አቶ ለማ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንትነትን ለቀው የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትርነት ቦታን ከያዙ በኋላ በፖለቲካው መድረክ ላይ ብዙም አይታዩም ነበር። ይህም በርካታ መላምቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኖ ነበር።

ለረጅም ጊዜ ድምጻቸው ጠፍቶ የነበሩት አቶ ለማ ዋና የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነው የተከሰቱት የኢህአዴግን መክሰም ተከትሎ አዲሱ 'ብልጽግና ፓርቲ' እውን ሲሆን ነበር። አቶ ለማ በውህደቱና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር እሳቤ ላይ ልዩነት እንዳላቸውን በፓርቲያቸው ውስጥ ተሰሚነት እንደሌላቸው በይፋ ሲገልጹ ግራ መጋባትን ፈጥሮ ነበር።

ይህም የአገሪቱን ፖለቲካ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሚመሩት መንግሥት ላይ ከባድ ቀውስ ያስከትላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ እንዲፈጠር አድርጎ ነበር።

አቶ ለማ ያሉበትን ሁኔታ ይፋ ካደረጉ በኋላ በመከላከያ ሚኒስትርነታቸው ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ለሥራ ወደ አሜሪካ ደርሰው ከተመለሱ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለእሳቸው ቅርብ በሆኑ የተለያዩ ሰዎች አማካይነት የሽምግልናና የማቀራረብ ጥረት ሲደረግ መቆየቱ ለጉዳዩ ቅርበት ያለቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።

በመጨረሻም አቶ ለማ ራሳቸው ወጥተው ባያረጋግጡም ወይም ባያስተባብሉም ፓርቲያቸውና አንዳንድ የፓርቲው ከፍተኛ ባለስልጣናት የተፈጠረው ልዩነት ላይ ውይይት ተደርጎ ከመግባባት ላይ መደረሱንና ከአዲሱ ፓርቲ አብረው ለመስራት መስማማታቸው ተነግሯል።