ለፑቲን ጥያቄ የሰነዘረችው ጋዜጠኛ ከሥራዋ ተሰናበተች

አሊሳ ያሮቪሰካይ

የፎቶው ባለመብት, Kremlin

ከቀናት በፊት የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን ጥያቄ የጠየቀችው ጋዜጠኛ አሊሳ ያሮቪሰካይ ከሥራ የመሰናበቷ ጉዳይ በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል።

ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከጥቂት ቀናት በፊት ባካሄዱት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነበር አሊሳ ለፕሬዝደንቱ ጥያቄዎቿን የሰነዘረችው።

ከጋዜጣዊ መግለጫው ከጥቂት ቀናት በኋላ ጋዜጠኛ አሊሳ በራሷ ፍቃድ ከሥራዋ እንደተሰናበተች ብትናገርም፤ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛዋ የሰነዘረችው ጥያቄ ባለሥልጣናትን ስላበሳጨ ከሥራዋ እንድትባረር አድርጓታል።

ከአምስት ቀናት በፊት ቭላድሚር ፑቲን በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ያማል የምትሰኘውን የሩሲያ ግዛት ወክለው ተሳታፊ ከነበሩት ጋዜጠኞች መካከል አሊሳ ያሮቪሰካይ አንዷ ነበረች።

ከያማል ግዛት ለመጡ ጋዜጠኞች ጥያቄ እንዲጠይቁ እድል ሲሰጥ፤ አሊሳ ማይክራፎኑን በመያዝ ለፕሬዝደንቱ ጥያቄዎቿን መሰንዘር ጀመረች። ከያማል ግዛት ጥያቄ እንዲጠይቅ በፕሬዝደንቱ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተመርጦ የነበረው አሊሳ ሳትሆን ሌላ ጋዜጠኛ ነበር።

አሊሳ በጥያቄዋ እርሷ ከመጣችበት ግዛት ግንባታቸው ተጀምሮ ያላለቁ መሰረተ ልማቶች እያስከተሉ ያሉትን ጉዳቶች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ለጉዳዩ ደንታ እንደሌላቸው ከተናገረች በኋላ፤ ይህ ችግር በሩሲያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ ለምን እንደማይታይ ጠይቃለች።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ፑቲን ለጋዜጠኛዋ ምላሽ ሲሰጡ፤ በቀጠናው ያሉት የመሰረተ ልማት ፕሮጄክቶች ወሳኝ የሆነ ትርጉም እንዳላቸው ጠቅሰው፤ መንግሥታቸው በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛዋ ተቀጥራ ትሰራበት የነበረው የመገናኛ ብዙሃን ተቋም በመጣችበት ግዛት አስተዳዳሪዎች በበላይነት የሚመራ እንደሆነ ተነግሯል።