#8 እሷ ማናት፡ "አፍሪካዊያንን ሚሊየነር ለማድረግ አስባለሁ"- ሐና ተክሌ

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

አትችይም የሚሉኝ ሰዎች ሁሌም ለሌላ ተጋድሎ ያነሳሱኛል።

ሐና ተክሌ እባላለሁ። አዲስ አበባ አብነት፣ ቀበሌ 28 አካበቢ ነው ተወልጄ ያደግሁት። እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ ግን ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄጄ ኑሮዬን በዚያ አድርጌያለሁ። ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ነኝ።

በ2004* ሂልኮ የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ነበርኩ። ሁሌም የራሴን ሥራ መስራት እፈልግ ስለነበር በርካታ መጽሐፍትን ሳነብ የሕይወቴን መስመር ቀየርኩ።

የሕይወት መስመሬ በትምህርት ብቻ አለመሆኑን ስረዳ የተለያዩ ነገሮችን በአማራጭነት መመልከት ጀመርኩ። ያኔ እጄ ላይ ከወደቀው እድል አንዱ ኔትወርክ ማርኬቲንግ ነው።

በተለይ እናቴ ያሳደገችኝ ብቻዋን መሆኑ ወደዚህ ሥራ እንድገባ ምክንያት ሆኖኛል።

እናቴ ስድስት ልጆች ነበሯት እኔ ከሦስቱ ጋር ነው ያደግሁት። አምስተኛ ልጇ ነኝ። ልጆቿን ለማኖር ለረዥም ጊዜ በሥራ የኖረችው ዱባይ ነበር።

ሁሌም የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ከትምህርት መልስ እናቶቻቸው ምሳ አዘጋጅተው፣ ቡና አጫጭሰው ሲጠብቋቸው እናታችን አጠገባችን ስለሌለችና ይህንን ማየት ባለመቻሌ አዝን ነበር።

እንደ ሌሎች ልጆች እናቶች ቤት ቡና ቀራርቦ እናቴ እንድትጠብቀን የማድረግ የልጅነት ሕልሜ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ኔትወርክ ማርኬቲንግ ስሰማ ልቤ ውስጥ የነበረው ሰርቼ ውጤታማ ብሆን እናቴን ከዱባይ አምጥቼ ቤት ስገባ ዘወትር ባገኛት የሚለው ሀሳብ ነው ያነሳሳኝ።

ከዚያም በዚሁ ሥራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጓዝኩ፤ ደቡብ አፍሪካ የሄድኩት በአጋጣሚ ነው። ለሁለት ሳምንት ለሥራ በሄድኩበት ነው እዚያው የቀረሁት። የመጀመሪያውን አንድ ዓመት ወጣ ገባ እያልኩ ቆየሁ። ከዚያ በኋላ ግን ጠቅልዬ እዚያው መኖር ጀመርኩ።

ወደ ደቡብ አፍሪካም የተጓዝኩት እዚያ ደንበኞችን ለማፈፍራት ነበር። በመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ጉዞዬ ቢዝነሱ ስኬታማ ሆኖ ሰፍቶ ነበር። እስከ 2009 ድረስም ስሰራ ቆይቻለሁ።

በኔትወርክ ማርኬቲንግ ውስጥ ከገንዘብ በተጨማሪም የአመራር፣ የተግባቦት፣ የሽያጭና አስተዳደር ክህሎቶችን አግኝቼበታለሁ። ኔትወርክ ማርኬቲንግ ብዙ አስተምሮኛል። ማግኘትና ማጣት ብዙ አስተምሮኛል።

በራስ መተማመኔን የጨመረውም እርሱን እየሰራሁ ነው። ይህ የሥራ ሕይወት የተለያዩ በሮች እንዳሉትና በየትኛውም መንገድ ብጓዝ ስኬታማ እንደምሆን ያየሁበትም ነው።

2009 ላይ ግን ይህንን ሥራ አቁሜ ሌሎች ሥራዎችን ጀመርኩ። ከሕንድ እቃዎችን እያስመጣሁ ለቸርቻሪዎች መስጠት ጀመርኩ። በእርግጥ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥራዎችንም ሰርቻለሁ። ትርፍና ኪሳራውን አይቼ በ2015 ላይ አቆምኩት።

በእርግጥ ሥራውን ያቆምኩት ስለከሰርኩ ነው ብል ይሻላል።

ትዳርና ሐና

2013 ላይ ትዳር መስርቼ ወዲያው የመጀመሪያ ልጄን ወለድኩ። ልጆች ስወልድ ለልጆቼ የተሻለ ጥሪት የመቋጠር ፍላጎት በብርቱ ፈተነኝ። ባለቤቴ ጋቦናዊ ሲሆን የህይወት እቅዱ በሙሉ ተምሮ ስኬታማ መሆን ነው። የሒሳብ ትምህርት ያጠና ሲሆን ያን ጊዜ ሦስተኛ ዲግሪውን እየሰራ ነበር።

ስንጋባ 35 ዓመቱ ነበር። እሱም 40 ዓመት ሳይሞላው ፕሮፌሰር ለመሆን በማለም እየጣረ ነበር።

የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ክፍያ ደሞዙን ሳሰላው ባሌ በሚያገኘው ገንዘብ ልኖረው የምፈልገው ህይወት ሩቅ መሆኑ ተሰማኝ።

ስለዚህ ከ2013 ጀምሮ የልቤን ፍላጎት ይዤ በየቀኑ አዳዲስ የንግድ ሀሳቦችን እመለከት ጀመር። ከዚያ እርሱ ከሥራ ወደቤት ሲመለስ ያገኘኋቸውን የንግድ ሀሳቦች እንመካከርባቸዋለን። ሁለተኛ ልጄን ከወለድኩ በኋላ ቢትኮይንን ተዋወቅሁ።

2015 ነሐሴ ወር ላይ ስለቢትኮይን ሰምቼ ለባለቤቴ ብነግረውም ሊቀበለኝ አልቻለም።

ስለቢትኮይን ለመጀመሪያ ጊዜ ልታስረዳኝ የሞከረችውን ልጅ ለስድስት ዓመት ልጅ እንደምታስረጂ አድርገሽ አስረጂኝ ብያት ብታስረዳኝም አልገባኝም ነበር።

ጎግል ላይ በቀላሉ መረዳት የሚቻልበት መንገድን ጠይቄ ያገኘሁት መረጃ ግን ረዳኝ።

ባለቤቴ የዘወትር ውትወታዬ ሲበረታበት አንድ ለሊት ቁጭ ብሎ ማንበብ ጀመረ። ባነበባቸው ጥናቶች ውስጥ የተሳተፉ ዩኒቨርስቲዎች፣ የተደረጉ ጥናቶች ቢዝነሱ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አሳዩት። በኋላ ትኩረት ልሰጠው እንደሚገባ ነገረኝ።

የፎቶው ባለመብት, Hanna Tekle Facebook Page

ከዚህ በኋላ ነው ቀላል የምለውንና አቅሜ የሚችለው ላይ የተሳተፍኩት። ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ 'ማይኒንግ' [በቢትኮይን ውስጥ ያለ ሥራ] ላይ መስራት ጀመርኩ።

በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርቼ ገና መስመር ሳይዝ ባለቤቴ በካናዳ ኦንታሪዮ ሪሰርች ኢንስቲትዩት የተመራማሪነት እድል አግኝቶ እኔና ልጆቼ ደቡብ አፍሪካ ቀርተን እርሱ ብቻውን እንዲሄድ ተስማማን።

በዚህ ተስማምተን እርሱ ካናዳ ሄዶ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ከሚያገኘው ገቢ ላይ ወደ ደቡብ አፍሪካ መላክ ነበረበት።

ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቢትኮይን ገንዘብ ማግኘት ጀመርኩ። በስድስት ወር ውስጥ የእርሱን የዓመት ደሞዝ ያህል ማግኘት ጀመርኩ። ከዚያ በኋላ ወደ ካናዳ የመሄድ ሀሳቤን ተውኩት።

ከስድስት ወር በኋላ ሊጠይቀን ሲመጣ ያለውን ለውጥ ተመለከተና ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ የካናዳ ሥራውን ጥሎ እኔን ለመደገፍ መጣ።

በዚህ ሥራ ውስጥ ከተሰማራሁ በኋላ በአንድ ዓመት ከግማሽ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ችያለሁ። ከዚያ በኋላም ቢዝነሱ እየሰፋ እና እየተጠቀምኩ ነው።

ሚሊየነር መሆን ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው መንገዱ ክፍት ነው። ልጅ ወልደው ተደራራቢ ኃላፊነት ላለባቸው በቀላሉ ሊሰሩት የሚችሉት ሥራ ነው። እኔ በሰው አገር እየኖርኩ፣ ሦስት ልጆች እያሉኝ፤ ሁሉም ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ፤ መስራት ከቻልኩ ሌሎችም መስራት ይችላሉ።

ለዚህ ሥራ ኢንተርኔትና ሀብታም የመሆን ፍላጎት እስካለ ድረስ መስራት ይቻላል።

አትችይም የሚሉኝ ሰዎች ሁሌም ለሌላ ተጋድሎ ያነሳሱኛል። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሀገሩን ቋንቋ አትናገሪም ያሉኝ፣ ሴት መሆኔን ያስታወሱኝ ሰዎች በአጠቃላይ ዛሬ ለደረስኩበት አነሳስተውኛል።

ባለቤቴ ቤት ውስጥ ከማርገዝና ከማጥባት ውጪ ሁሉንም ነገር ያግዘኛል፤ ይደግፈኛል። በዚህም እድለኛ ነኝ።

ገንዘብ ለሁሉም ነገር መፍትሔ አይደለም። ነገር ግን ገንዘብ ሁሉንም ነገር ያቀላል። ስለዚህ ገንዘብ ሁሌም ለማግኘት ጠንክሬ እሰራለሁ። እንደ አፍሪካዊ የእኔ ሕይወት ሲቀየር የሌሎችም ሕይወት ስለሚቀየር የአንድን ሰው ሕይወት ለመለወጥ ጠንክሬ ነው የምሰራው። ብዙ አፍሪካዊያንን ሚሊየነር ለማድረግ አስባለሁ።

ቢትኮይን ምንድን ነው?

ቢትኮይን ልክ እንደ ዶላር እንደ ዩሮ ሁሉ ገንዘብ ነው። ሌላው ቢትኮይንን ከአንድ ሰው ወደ ሌላው በቀላሉ ዋጋው ሳይሸራረፍ ማስተላለፍ ይቻላል። ቢትኮይን ለመላክ የሦስተኛ አካል ጣልቃ ገብነትን አስወግዷል።

እኔ ቢትኮይን ማይኒንግ ላይ ከተሰማራሁ በኋላ ሁሌም ለሌሎች የምነግረው ቢትኮይንን ገዝተው ማስቀመጥ እንደሚችሉ፣ ቢትኮይን ንግድ ላይ የመሰማራት እድል መኖሩን አልያም ንግዳቸውን በቢትኮይን መገበያየት እንደሚችሉ ነው።

ይህ ለሁሉም ሰው ያለ እድል ነው። ግን በጥንቃቄ መስራት ያስፈልጋል። በዓለም ላይ በርካታ አጭበርባሪዎች ስላሉ በሚገባ አጥንቶ መግባት ያስፈልጋል። ሚሊየነር መሆን ይቻላል ስል በአንድ ጀምበር መሆን ይቻላል እያልኩ አይደለም። ጠንክሮ መስራትን ይጠይቃል።

እኔ የተሰማራሁበት ቢትኮይን ማይኒንግ ይባላል። ቢትኮይን ማይኒንግ ገንዘብ ማተም እንደማለት ነው፤ ቢትኮይን ማተም ነው። ለዚህ ሁሉ ግን ጠንከር ያለ ገንዘብ እንዲሁም ታማኝ አጋር ማግኘት ያስፈልጋል።

እኔና ባለቤቴ 2015 ላይ 'አቺቨርስ ክለብ አካዳሚ' የተሰኘ ተቋም አቋቁመን ክሪፕቶከረንሲ አካዳሚ እና ኔትወርክ ማስተማር ጀመርን። ይህንንም ከፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ ጋር በትብብር ነው የምንሰራው።

በአካዳሚያችን ፋንዳሜንታል ኦፍ ብሎክ ቼይን፣ ክሪፕቶከረንሲ ኤንድ ክሪፕቶ ፋይናንስ፣ ብሎክ ቼይን ፎር ቢዝነስን የተሰኙ ኮርሶች እናስተምራለን።

እኔ ደግሞ በአቺቨርስ ኔትወርክ በኩል ወደ ተለያዩ አገራት እየሄድኩ ልምዴን አካፍላለሁ።

ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እንሰራለን። የምንሰራው በአፍሪካ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለማችን 33 አገራት ውስጥ ነው። እስካሁን 30 የሚሆኑ ሰዎች በሥራቸው ሚሊየን ዶላር እንዲያገኙ አድርገናል። ከእነዚህ ሰዎች መካከልም በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው የሚሰሩ አንዳንዶቹም የለቀቁ ይገኙበታል።

በአፍሪካ ውስጥ በዚህ ትምህርት ሰፊውን ሥራ እየሰራን ነው።

አሁን መቀመጫውን ፖላንድ ካደረገ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርመን እየሰራን ነው። እኔ ሰዎችን አስተምራለሁ፤ አፍሪካ ውስጥ ላለ ሰው ትልቅ እድል ነው። ማንም ሰው ቢሰማራበት ውጤታማ ሊሆን ይችላል።

*ሁሉም የዘመን አቆጣጠሮች በአውሮፓዊያን ነው

እሷ ማናት? የሚለው ጥንቅራችን ያሰቡበትን ዓላማ ለማሳካት ብዙ ውጣውረዶችን ያሳለፉ ሴቶችን ታሪክ የምናስቃኝበት ነው።