በጋምቤላ ክልል በመንግሥት መኪና የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በቁጥጥር ስር የዋለ ህገወጥ ጦር መሳሪያ

የፎቶው ባለመብት, ፎቶ ፋይል- Fana Broadcasting Facebook

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ሲያዘዋውሩ ያገኛቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ኦፒያንግ ኦቻን ለቢቢሲ ገለፁ።

ሕገ ወጥ መሳሪያዎቹ የተያዙት በግልና በመንግሥት መኪኖች መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነር ኦፒያንግ መኪናውን ለአጣቢ ሰጥቶ የሚያጥበው ልጅ ያለ ሹፌሩ እውቅና ይዞ መሄዱን ይናገራሉ።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ኦታዎ ኦኮት በበኩላቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት 12 ክላሽንኮቮችና 471 ጥይቶች መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አክለውም አቶ ኦታዎ የመንግሥት መኪናውን ሲያሽከረክር የነበረው የክልሉ አፈ ጉባኤ ሹፌር ነው ብለዋል።

የመንግሥት መኪና ሲያሽከረክር የነበረው ግለሰብ ያለ ኃላፊው እውቅና ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ መኪናውን ይዞ መውጣቱን ተናገሩት የፀጥታ ኃላፊው፣ በቁጥጥር ስር የዋለው የግል መኪና ግን ማለዳ 12 ሰዓት አካባቢ መያዙን ያስረዳሉ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኞ ታህሳስ 13 ምሽት መሆኑንም ገልፀዋል።

መሳሪያውና ጥይቶቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ኢታንግ አካባቢ በሚገኝ ኬላ ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኦታዎ እስካሁን ድረስ ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ምርመራ በሒደት ላይ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ አስፈላጊው ምርመራ እንደተጠናቀቀ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ገልፀዋል።

በጋምቤላ ክልል በላፉት ሶስት ወራት ብቻ 47 ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች ወደ ክልሉ ሲገቡ መያዛቸውን የጠቀሱት አቶ ኦታዎ ኦኮት ትናንት ከተያዙት ጋር በአጠቃላይ 59 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች መያዛቸውን አስረድተዋል።

"ሕገ ወጥ መሳሪያዎቹ የሚመጡት በደቡብ ሱዳን በኩል ነው" በማለት የተናገሩት ደግሞ ኮሚሽነር ኦፒያንግ ናቸው።

በኢትዮጵያ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር እጨመረ መምጣቱንና የጸጥታ ኃይሎችም ከፍተኛ መጠን ያለቸውን መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ በተለያዩ ጊዜ መዘገቡ ይታወሳል።