"የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ ላይ የሚለወጡ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ" የጠ/ሚ የኢኮኖሚ አማካሪ

ዶ/ር ነመራ ገበየሁ

የፎቶው ባለመብት, NEMERA G. MAMO FB

በኢትዮጵያ እየተደረጉ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከምዕራቡና ከአረቡ ዓለም የገንዘብ ድጋፍና ብድር እያገኘች ነው። እየተደረገ ካለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ 'አገር በቀል ኢኮኖሚ' የሚል አካሄድን እየተከተለ መሆኑንም መንግሥት እየገለፀ ነው።

በቅርቡም የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ለኢትዮጵያ የ2.9 ቢሊዮን ዶላር የብድር ድጋፍ ለማድረግ ተስማምቷል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ነመራ ገበየሁ ማሞን በአገሪቱ እየተደረገ ስላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ስለ አይኤምኤፍ ብድር ጠይቀናቸዋል።

ቢቢሲ፡ አይኤምኤፍ ብዙ ጊዜ የሚያበድረውም ሆነ የእርዳታ ድጋፍ የሚያደርገው ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ነው። ኢትዮጵያስ የ2.9 ቢሊዮን ዶላሩን ብድር በምን አግባብ አገኘች?

ዶ/ር ነመራ፡ እውነት ነው እነ አይኤምኤፍ ከአሁን በፊት ብድር የሚሰጡት ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ነው። ቅድመ ሁኔታው ደግሞ ከማክሮ ኢኮኖሚ እስከ ታች ያሉ ነገሮችን የሚነካ ነው።

አሁን የኢትዮጵያን ለየት የሚያደርገው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ከአንድ ዓመት በላይ ባሉት ጊዜያት ብዙ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን እያካሄደች፤ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ሃገር በቀል የሆነ የለውጥ መንገድ ስትተገብር ነበር። አይኤምኤፍ ደግሞ ለእንደዚህ ያሉ ነገሮች እርዳታ የማድረግ አካሄድ አለው። በዚህ መንገድ መጥተው ነው ኢትዮጵያን እንረዳለን ያሉት።

ስለዚህ እነሱ ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ የለም። ኢትዮጵያ በመንግሥት እጅ ያሉ ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን ለመፍታት የወሰነቸው አይኤምኤፍ ከመምጣቱ በፊት ነው። አሁን ያለው መንግሥት ማሻሻውን የጀመረው ቀድሞ ነው። ከዚያ እነሱ ይሄንን ሀሳብ እንደግፋለን ብለው ነው ብድሩን ሊሰጡ የቻሉት።

ቢቢሲ፡ ለአይኤምኤፍ ተብሎ ባይሆንም ቅድመ ሁኔታዎቹ በኢትዮጵያ በኩል ተሟልተው ነበር ማለት እንችላለን?

ዶ/ር ነመራ፡ በትክክል፤ በእርግጥ በአይኤምኤፍም በዓለም ባንክም እነዚያ በ1980 እና 90 ዎቹ የነበሩት የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራሞች Structural Adjustment Policy) የሉም፤ እየላሉ መጥተዋል። ከነበሩ ልምዶች ተነስተው ነገሮችን ለቀቅ እያደረጉ የመጡበት ሁኔታ ነው ያለው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደግሞ ከግብር መሰብሰብ ጀምሮ እስከ የውጭ ምንዛሪ ያሉ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ችግር ውስጥ ስለሆነ ያንን መቅረፍ ግዴታ ነበር። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተወሰደውን ተነሳሽነት ለመደገፍ ነው እነ አይኤምኤፍ የመጡት።

ስለዚህ በሚቀጥሉት ከ3 እስከ 5 ዓመት የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ፍጥነት የሚወስነው የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ ማንም አደለም። ኢትዮጵያ ባላት የሰው ኃይል እና ሌሎች ሁኔታዎች ፍጥነቱን ጠብቃ መሄድ አለባት የሚለው ጠንካራ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠውም በኢትዮጵያ መንግሥት ነው።

በሌላ በኩል አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ደግሞ እርዳታ ሲሰጡ ግልጽነት ይፈልጋሉ፤ እውነት ይሄ ለውጥ በሚፈለገው አቅጣጫ እየሄደ ነው ወይ? የሚለውን ማወቅ ይፈልጋሉ። እዚህ ላይ ከእነሱ ጋር የሚሰራበት ሁኔታ ይኖራል ግን ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ እንደሚባለው እጅ ለመጠምዘዝ ኢትዮጵያ ላይ አቅም የሚኖራቸው አይመስለኝም።

ቢቢሲ፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአይኤምኤፍ የሚያገኘውን ብድር በሚፈልገው ሁኔታ ወጪ የማድረግ ነጻነት ይኖረዋል?

ዶ/ር ነመራ፡ አዎ፤ ግን እንደፈለገ ሲባል መንግሥት የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት ስላለበት፤ የራሱን ቀዳሚ ሥራዎችን በመለየት ግልጽነት ባለው መንገድ ለሚፈለገው አላማ ገንዘቡን የማዋል ሙሉ ስልጣን አለው።

ለምሳሌ ፕራይቬታይዜሽን ላይ የተለያዩ ሥራዎች ይኖራሉ። ድርጅቶቹ ላይ ለውጥ የማድረግ፣ አቅም መገንባት የመሳሰሉ ሥራዎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው።

ወደ በጀትም ከሄድን፤ ባለፉት 50 ዓመታት ሲያከራክር የነበረው ጉዳይ መንግሥት ወጪዎችን መቀነስ አለበት የሚለው ነው። አሁን ያለው የኢኮኖሚ ለውጥ ትኩረት ያደረገው የመንግሥትን ግብር የመሰብሰብ አቅም ማሳደግ ላይ አንጂ ወጪ መቀነስ ላይ አይደለም።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ለውጥ ማድረግ፣ ከመንግሥት ወደ ግል ማዞርም ላይ የሚሰሩ ብዙ ሥራዎች አሉ። ለዚህም የገንዘብ ድጋፍ ስለሚያስፈልግ እዚህ ላይ ይውላል እርዳታው።

ሌሎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል የተባሉ እንደ ግብርናና ቱሪዝም ያሉ ዘርፎችም አሉ፤ ገንዘቡ እዚህ እዚህ ላይ ነው የሚውለው። መጨረሻ ላይ ግን ይህ ብር የኢትዮጵያ ተወዳዳሪነትን በማጎልበት ወደ ውጭ ሃገር የምትልከውን ምርት በማሳደግ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት መቅርፍ አለበት፣ ሃገር ውስጥ ያለውን የሥራ ፈጠራና የገቢ እድገት ማረጋገጥ አለበት፤ ምክንያቱም ድህነትን ለመቀነስ ሁለቱም ቀዳሚ ጉዳዮች ናቸውና።

ቢቢሲ፡ መንግሥት እየተከተለ ያለው አካሄድ ወጪውን ለመቀነስ የሚያደርጋቸውን ድጎማዎች ማንሳት ሳይሆን የታክስ ገቢውን ማስፋት እንደሆነ ገልፀውልኛል። ሰሞኑን ለፓርላማ የቀረበው ኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ የዚህ ውጤት ነው?

ዶ/ር ነመራ፡ አዎ፤ መንግሥት ድህነት ለመቀነስና መሰረት ልማት ለማስፋፋት የሚያርገው የገንዘብ ወጪ ላይ ትልቅ ለውጥ አይኖርም፤ ግን ኢትዮጵያን የሚያስቸግሯት እንደ ሙስናና የሃብት ብክነትን የመሳሰሉ ነገሮች ላይ ትልቅ ለውጥ እየተካሄደ ነው።

ኢትዮጵያ ላይ እንደ ትልቅ አጀንዳ ተወስዶ እየተሰራ ያለው ነገር ግን፤ ከተቋም ጀምሮ እስከ ፖሊሲ ግብር መሰብሰብ ላይ ነው፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አቅም ማሳደግ ላይም ብዙ ሥራ እየተሰራ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥም ግብር የመሰብሰብ አቅም እያደገ መጥቷል።

ታክስን በተመለከተ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታዩ የፖሊሲ ክፍተቶች አሉ፤ እዚህ ላይም ማሻሻያ እየተደረገ ነው። ወደ ፓርላማ የተላከው የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅም ከዚህ አንፃር የሚታይ ነው። አገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጭ የሚገቡ አንዳንድ ምርቶች ላይ የንግድ ምህዳሩን በማይጎዳ መልኩ የመንግሥትን ግብር የመሰብሰብ አቅም ለማሳደግ የሚደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች አሉ።

ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአፍሪካ ደረጃ ጭምር ዝቅተኛ ግብር በመሰብሰብ ነው። ስለዚህ እዚህ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ትልቅ ሥራ እየተሰራ ሲሆን እርምጃው ኤይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ከሚያተኩሩባቸው ነገሮች ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።

ቢቢሲ፡ እየወጡ ባሉት መረጃዎች መሰረት ረቂቅ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ እንዳለ ከፀደቀ የብዙ ነገሮችን ዋጋ የማናር አዝማሚያ ይኖረዋል የሚል ትልቅ ስጋት አለ። እርሶ እንዴት ነው አዋጁን የሚያዩት?

ዶ/ር ነመራ፡ ምን አይነት ጫና ይኖረዋል የሚለውን አሁን መናገር ትንሽ ይከብደኛል። ረቂቅ አዋጁ ገና ብዙ መንገድ ያልፋል፤ ብዙ የሚቀየሩ ነገሮችም ይኖራሉ።

ለምን አስፈለገ የሚለው ላይ ግን፤ ከምንልከውና ከምናስገባው ምርት ጋር በተያያዘም መንግሥት በጣም ዝቅተኛ ገቢ እየሰበሰበ ስላለ መሞላት ያለባቸው ክፍተቶች ስላሉ ነው ፖሊሲው የመጣው። ጫናው ግን ደሃው የህብረተሰብ ክፍል ላይ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረጋል።

የፎቶው ባለመብት, NEMERA G. MAMO FB

ቢቢሲ፡ በአጠቃላይ አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ብድር የሰጠው ፕራይቬታይዜሽንን ለማሳለጥ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን?

ዶ/ር ነመራ፡ የአይኤምኤፍ ብድር ፕራይቬታይዜሽን ላይ፣ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ የሚደረጉ አንዳንድ የፋይናንስ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ገንዘብ ስለሚጠይቁ እዚያ ላይ ይውላል።

ነገር ግን ይህ ዋነኛው ምክንያት ነው፤ ይሄኛው ሁለተኛ ነው የምልበት መመዘኛ ስለሌለኝ፤ ፕራይቬታይዜሽን ዋነኛው አጀንዳ ነው ማለት ይከብደኛል። ግን ሁለት ነገሮች ላይ ማለትም የመንግሥት የልማት ተቋማትን ማሻሻል እንዲሁም ወደ ግል ይዞታ ማዞር ላይ ትልቅ ሥራ እየተሰራ ነው።

ቢቢሲ፡ ኢትዮጵያ ትልቅ የእዳ ጫና ያለባት አገር ናት፤ ከዚህ አንፃር የተጨማሪ ብድር አስፈላጊነት እንዴት ይታያል ?

ዶ/ር ነመራ፡ የብድር ጫና የሚባለው መጠኑ አይደለም። ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ምጣኔ አንጻር ሲታይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ብድሩ 60 በመቶ ጠቅላላይ የሀገር ውስጥ ምርት አይሆንም፤ ስለዚህ ይህ በራሱ ችግር አደለም።

አሁን ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ያለው ብዙዎቹ የውጭ ብድሮች፤ በትልቅ የወለድ መጠን በአጭር ጊዜ የሚከፈሉ ሆነው መምጣታቸው ነው። የኢትዮጵያን ወጪ ንግድ ካየን ግን ዶላር የማግኘት አቅሙ በጣም ዝቅተኛ ነው። ችግሩ እዚህ ጋር ነው ያለው።

ከአይኤምኤፍ፣ ከአለም ባንክ፣ ከአውሮፓ ሕብረትና ሌሎች አገራት እየተደረጉ ያሉትን የብድር ድጋፎች በዝቅተኛ ወይም በዜሮ የወለድ መጠን የሚወሰኑ ናቸው። የምንመልስበት ጊዜም በረጅም ጊዜ ነው።

የውጭ ምንዛሪ ላይ ጫና ሳይፈጥር ነው የሚከፍለው፤ ስለሆነም ከዚህ በፊት በከፍተኛ ወለድ ከቻይና የወሰድናቸውን ብድሮችም ወደ ዝቅተኛ ወይም ዜሮ ወለድ እንዲቀየሩ እያደረግን ነው። ይህ ኢትዮጵያ ላይ ያለውን ጫና እየቀነሰ ይሄዳል ከዚህ ወዲህም አካሄዱ በዚህ አንፃር ይሆናል።

ቢቢሲ፡ መንግሥት እያደረገው ያለውን ማሻሻያ ተከትሎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብድርና ድጋፍ እየተገኘ ነው። ብድሩና እርዳታው የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት እና ሌሎች የኅብረተሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዱት እንዴት ነው?

ዶ/ር ነመራ፡ የዚህ ሁሉ ማሻሻያ ዋና አላማ የግል ዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ ነው። የዚህ ዘርፍ ምርታማነት ካላደገ ኢኮኖሚው ውስጥ የሥራ ፈጠራ እድሎችን ማስፋት አይቻልም። ኢትዮጵያን አንቆ የያዛት ትልቅ ነገር የግል ዘርፉ ምርታማነት ዝቅተኛ መሆን ነው።

የጠቀስናቸው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መጨረሻ ግብ የግሉን ዘርፍ ምርታማነት ማሳደግ ነው። በግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ፤ በተለይ ደግሞ በአግሮ ኢንዳስትሪ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

ለእነዚህ ዘርፎች ቅድሚያ መስጠት ያስፈለገው የሥራ መፍጠር አቅማቸው ታይቶ ነው። ጊዜ ሊወስድ ቢችልም በአጭርና መካከለኛ ጊዜ የሚደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ኅብረተሰቡን እንዲያግዙ የተቀመጡ ግቦች አሉ።

ቢቢሲ፡ አገር በቀል ኢኮኖሚ ምንድን ነው?

ዶ/ር ነመራ፡ የተለየ የኢኮኖሚ እሳቤ አይደለም ይልቁንም አሁን የምንከተለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመደመር እሳቤ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብን በመጠቀም ያለብንን የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ችግሮች መፍታት አለብን የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ እሳቤ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፈው ሃያ ወራት እየተደረገ ያለው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ለውጥ መነሳሳት እና እሳቤው የመጣው ከዚሁ አንፃር ከአገር ውስጥ ነው። ለውጡ የውጭ ግፊት የወለደው ሳይሆን ከራስ የመጣ ስለሆነ ነው አጠቃላይ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተባለው።

ቢቢሲ፡ ዋና ዋና ተብለው ሊገለፁ የሚችሉ የአገር በቀል ኢኮኖሚ እሳቤ መገለጫዎች አሉ?

ዶ/ር ነመራ፡ ዋናው ነገር እሳቤው፣ ፍቃደኝነትና ተነሳሽነቱ የመንግሥት መሆኑ ነው። የኢኮኖሚ ጎኑን ብቻ ካየን ግን ሦስት ዋና ነገሮችን ይዞ ነው የተነሳው።

የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር በጣም በሚያስፈራ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። የብድር ጫናው፣ የወጪ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ፣ የወጪ እና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን የፈጠረው መዛባት ትልቅ መሆን፣ በአገሪቱ የገንዘብ ፖሊሲ ምክንያት የገንዘብ ሥርዓቱ በጣም የቀጨጨ እንዲሁም ቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል ያለው ሚዛንም አስፈሪ ነበር፤ የሥራ አጥነትና የዋጋ ግሽበትን ካየን ነገሮች በጣም ከባድ ነበሩ።

የግል ዘርፉም በብዙ ማነቆዎች የተያዘ ነው የሚያበረታታው ነገር የለም። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ከግንዛቤ ገብተው አገር በቀል ኢኮኖሚው ትኩረት ያደረገባቸው ዋንኛ ነገሮች ማክሮ ኢኮኖሚ ማኔጅመንቱ፣ የቢዝነስ ተነሳሽነቶችን ማምጣትና የኃይል እንዲሁም የሎጀስትክ ዘርፍ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ናቸው። በዚህ ረገድ የማዕድን እና የቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ትኩረት የሚደረግባቸው ናቸው።

ቢቢሲ፡ ትልልቅ የውጭ ብድሮች በተቋማት የማስፈፀም አቅም ማነስና በሙስና የታለመላቸውን ዓላማ ሳያሳኩ ሲቀሩ ታይቷል። አሁን ኢትዮጵያ እያገኘች ካለችው ብድር ጋር በተያያዘ ይህ እንዳይሆን የሚያስችል ሥርዓት አለ?

ዶ/ር ነመራ፡ እውነት ነው ይህ ትልቅ ስጋት ነው። የኢትዮጵያ ተቋማዊ ሥርዓት ጥራትና አቅም ማነስ በሙስናም ይሁን በሌላ ለሕዝብ ሃብት ብክነት ምክንያት ናቸው። አሁን ብዙ እየተባለ ያለው ስለ ፕራይቬታይዜሽን ብቻ ሆነ እንጂ በለውጡ እየተሰራ ያለው ትልቅ ነገር በመንግሥት እጅ ያሉና ትልቅ ሙስና እየተሰራባቸው ያሉ ድርጅቶች አስተዳደር ላይ ማሻሻያ ማድረግ ነው። [የማሻሻውን ውጤት ማየት ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም።]

ቢቢሲ፡ በመሰረተ ልማት ግንባታ በብድርም ሆነ በንግድ ኢትዮጵያ ጠንካራ ትስስር የነበራት ከቻይና ጋር ነው። በአሁኑ ወቅት በተለይም ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ምዕራቡና አረቡ ዓለም አዙራለች። የቻይና አጋርነት እያበቃ ነው?

ዶ/ር ነመራ፡ አንድ አገር ያላት የብድር፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ሁለት መልክ አለው። አንዱ በማስፋት፤ ሁለተኛው በጥልቀት መሄድ ነው።

ከቻይና ጋር ባለፉት 15 ዓመታት በጣም በጥልቀት ነው የሄድንበት፤ አሁንም ኢትዮጵያ ይህንን ትታ ሌላ መፈለግ ላይ አይደለም ያለችው። ያለው ነገር ላይ መጨመር ማስፋት ነው እየተደረገ ያለው።

አዲስ ምንጭ፣ አዲስ የንግድ አጋር የማፈላለግ ሥራ ነው እየተሰራ ያለው። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ከምዕራቡና ከአረቡ ዓለምም ጋር ጥሩ ትስስር እየፈጠረች ነው። ቻይና አሁንም ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አላት።