ቻይናዊቷ የዘር እንቁላሏን አላስቀምጥም ያላትን ሆስፒታል ከሰሰች

ቴሬሳ ዡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አንዲት ቻይናዊት የዘር እንቁላሏን በማቀዝቀዝ ለረዥም ጊዜ እንዲያስቀምጥላት የጠየቀችው ሆስፒታል ባለማግባቷ ምክንያት ጥያቄዋን ውድቅ በማድረጉ ክስ መሰረተች።

ቴሬሳ ዡ የተባለችው ግለሰብ በሥራዋ ላይ ለማተኮር ባላት ፍላጎት የተነሳ የዘር እንቁላሏ ለጊዜው በሆስፒታል እንዲቀመጥላት ለመጠየቅ ቤጂንግ ውስጥ ወደሚገኘው የጽንስና የማህጸን ሆስፒታል የሄደችው ባለፈው ዓመት ነበር።

የ31 ዓመቷን ጋዜጠኛ ጥያቄ የሰሙት የሆስፒታሉ ሠራተኞች ግን እንቁላሎቿን ከማስቀመጥ ይልቅ ልጅ እንድትወልድ ጠይቀዋት ነበር።

እሷ እንዳለችው ከዚያም ለሆስፒታሉ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዳለገኘ ተነግሯታል።

"ወደ ሆስፒታሉ የሄድኩት ሙያዊ አገልግሎት ለማግኘት ነበር፤ ነገር ግን የገጠኝ ሥራዬን ትቼ መጀመሪያ ልጅ እንድወልድ የሚመክር ሰው ነው" ስትል ዡ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግራለች።

ሰኞ ዕለትም ቤጂንግ ውስጥ የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ዡ በሆስፒታሉ ላይ ያቀረበችውን ክስ የሰማ ሲሆን ጉዳዩም እልባት እስኪያገኝ በርካታ ወራትን ሊወስድ እንደሚችል ተነግሯል።

በተጨማሪም በቻይና የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ዋነኛ መነጋገሪያ ከመሆኑም በተጨማሪ በርካቶች ለግለሰቧ ያላቸውን ድጋፍ እየገለጹ ነው።

በተፈጥሮ የሴቶች የዘር እንቁላል እድሜ እየገፋ ሲሄድ እየተዳከመ ስለሚሄድ በኋለኛ እድሜያቸው ልጅ ለመውለድ አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል።

በአሁኑ ወቅት ቻይና ውስጥ እንቁላልን በማቀዝቀዝ ለማቆየት የሚፈልጉ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን የገንዘብ አቅሙ ያላቸው ሴቶች ደግሞ ህክምናውን ለማግኘት ወደ ባሕር ማዶ አገራት እስከመጓዝ ደርሰዋል።

ከስድስት ዓመት በፊት ታዋቂዋ የፊልም ተዋናይት ዡ ጂንግሊ ዘጠኝ እንቁላሎቿ ተጠብቀው እንዲቆዩ ማስደረጓን ገልጻለች። ለዚህም በ39 ዓመቷ ወደ አሜሪካ ሄዳ አስፋለጊውን ህክምና ማድረጓ ተነግሯል።

ቴሬሳ ዡም ወደ ውጪ አገር ሄዳ እንቁላሏን ለማስቀመጥ ብታስብም ዋጋው የሚቀመስ እንዳልሆነ ተናግራለች። በዚህም አገልግሎቱ ታይላንድ ውስጥ ከ14 ሺህ ዶላር በላይ እንዲሁም ከ28 ሺህ ዶላር በላይ ደግሞ አሜሪካ ውስጥ ያስወጣል።

ቻይና አስገዳጁን የአንድ ልጅ ፖሊሲዋን ከአራት ዓመት በፊት ያነሳች ቢሆንም ከወሊድ ጋር ተያያዘ አንዳንድ ክልከላዎች ግን አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ያላገባች ሴት የዘር እንቁላሏን ለወደፊት ጥቅም በማቀዝቀዣ ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ አትችልም።

ቻኦ ዊ የተባሉት የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ ስለጉዳዩ በሰጡት ምላሽ ላይ ተቋማቸው መንግሥት ላወጣውን ደንብ ተገዢ ከመሆን ውጪ የፈጸመው ጥፋት የለም ማለታቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።