የጃፓን ፓርላማ አባል ከአቋማሪዎች ጉቦ ተቀብለዋል በሚል ተያዙ

ካሲኖ የሚጫወቱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የጃፓን ገዢ ፓርቲና የአገሪቱ ምክር ቤት አንድ አባል በቁማር ላይ ከተሰማራ ድርጅት 34 ሺህ ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ጹካሳ አኪሞቶ እስካለፈው ጥቅምት ወር ድረስ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስርት ሺንዞ አቤ የካቢኔ አባል ሆነው በሰሩበት ጊዜ መንግሥት ለካሲኖ ቁማር ቤቶች ፈቃድ ለመስጠት የነበረውን ዕቅድ በበላይነት ሲከታተሉ ነበር።

የ48 ዓመቱ የምክር ቤት አባል ምንም የፈጸሙት ወንጀል እንደሌለና ስልጣናቸውን ተጠቅመው ለማንም ውለታ እንዳላደረጉ ተናግረዋል።

ዘገባዎች እንዳመለከቱት የፓርላማ አባሉ እስር ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ከካሲኖ ቁማር ጋር ያላቸውን አወዛጋቢ ፖሊሲ ሊያወሳስብባቸው ይችላል።

ስሙ ያልተጠቀሰ አቋማሪ ድርጅት በካሲኖ ቁማር ላይ ለመሰማራት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ለማድረግ በሦስት ሰራተኞቹ በኩል የቀረበላቸውን ገንዘብ አኪሞቶ ተቀብለዋል ሲል አቃቤ ሕግ ከሷል።

ገንዘቡን ሰጥተዋል የተባሉት ሦስቱ ሰዎችም ዛሬ በቁጥጥር ስር መዋላቸው አቃቤ ሕግ አመልክቷል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘም ከጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ሊብራል ዴማክራቲክ ፓርቲ የምክር ቤት አባል የሆኑት የታካኪ ሺራሱካ ቢሮዎች መፈተሻቸውን የጃፓን መገናኛ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

መንግሥት የካሲኖ ቁማር ቤቶች መከፈት የተዳከመውን የጃፓንን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እንደ አንድ አማራጭ ይመለከተዋል።

ለዓመታት ከዘለቀ ጠንካራ ክርክር በኋላ የጃፓን ፓርላማ የካሲኖ ቁማር በሆቴሎችና በስብሰባ ማዕከላት ውስጥ እንዲካሄድ የፈቀደ ቢሆንም፤ እስካሁን ግን ለማንም ፈቃድ አልተሰጠም።

ጃፓን ውስጥ ቁማር የማጭበርበር ያህል የሚታይ ሲሆን፤ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተው የካሲኖ ቁማር ቤቶች መከፈትን በርካቶች ይቃወሙታል።