የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈትን መነሻ ያደረገው ፌስቲቫል ዛሬ ይጀመራል

የአዲስ የቪድዮ ሥነ ጥበብ ፌስቲቫል

የፎቶው ባለመብት, AVAF

መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ. ም የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በይፋ ሲከፈት፤ ለዓመታት የተነፋፈቁ ቤተሰቦች በዓይነ ሥጋ ለመተያየት የበቁበት፣ ለዘመናት ያልተገናኙ ወዳጆች ዳግም የተቃቀፉበት ዕለት ነበር።

ምንም እንኳን ድንበር ምድራዊ እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ የሚሰፋና የሚጠብ ቢሆንም፤ ዓለም ላይ 'ከዚህ ወንዝ ወዲህ የኔ፣ ከዚያ ድንጋይ ወዲያ ያንቺ' በሚል ሳቢያ ብዙዎች ተዋድቀዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች የሁለቱ አገራት ጦርነት፤ ከዚያም ጦርነትም ሰላምም ያልነበረበት ሁኔታ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው የነጣጠለ ነበር።

የድንበሩ መከፈት ብስራት ሲሰማ፤ የበርካቶችን ስሜት የነኩ ፎቶዎች እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ምስሎችም በመገናኛ ብዙኀን ተሰራጭተዋል። እናትና ልጅ፣ ወንድማማቾች፣ ጓደኛሞች፣ የቀድሞ ጎረቤታሞች. . . ሲገናኙ የሚያሳዩ ምስሎች ለሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ግብዓት ሆነውም ነበር።

የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ከተከፈተ ከወራት በኋላ የድንበሩ የተለያዩ መስመሮች ቢዘጉም እንኳን፤ መከፈቱ የፈጠረውን ስሜት በመመርኮዝ የተዘጋጀው አዲስ የቪድዮ ሥነ ጥበብ ፌስቲቫል ዛሬ ታህሳስ 16፣ 2012 ዓ. ም. ይከፈታል።

በየሁለት ዓመቱ የሚዘጋጀው ፌስቲቫሉ ዘንድሮ ሦስተኛ ዙሩን ይዟል። መነሻውን የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈት ቢያደርግም፤ በመላው ዓለም ከድንበር ጋር የተያያዘ ታሪክን ለማስቃኘትም ያለመ ነው። ለዚህም ከ11 አገራት የተውጣጡ 18 የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ተጋብዘዋል።

የጋራ ድንበር ወይም 'Mutual Periphery' በተሰኘው ፌስቲቫል የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን በተመለከተ ሥራቸውን የሚያሳዩ ሦስት ኢትዮጵያዊያን ክብሮም ገብረመድህን፣ ህሊና መታፈሪያ እና ቴዎድሮስ ክፍሌ ናቸው።

የቴዎድሮስ ቪድዮ፤ የድንበሩን መከፈት ተከትሎ በፌስቡክ ላይ ብዙዎች የተጋሯቸው የደስታ መልዕክቶች ላይ ያተኮረ ነው። ከሌላ አገር በፌስቫሉ ላይ ከሚቀርቡ ሥራዎች በዩክሬናዊ አርቲስት የተሠራውና ወጣቶች በምን መንገድ ጦርነትን እንደሚገልጹ የሚያሳያው ይጠቀሳል።

የአዲስ የቪድዮ ሥነ ጥበብ ፌስቲቫል መስራችና አዘጋጅ እዝራ ውቤ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ የድንበር ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ የኢትዮጵያ እና የኤርትራን መነሻ አድርጎ የብዙ አገሮችን ተሞክሮ በሥነ ጥበብ መግለጽ ይቻላል።

"አንዱ ከማሌዥያ ሌላው ከናይጄሪያ ቢሆንም አንድ ናቸው። በሥነ ጥበብ እንዴት ተመሳሳይ ድልድይ መፍጠር እንደሚቻል ማሳየት ይቻላል" ሲልም ያስረዳል።

ፌስቲቫሉ ላይ የሚታዩት ቪድዮዎች ልዩነት ባለበት ቦታ መቻቻል እንዲሰፍን፣ ሰላም ቅድሚያ እንዲሰጠው እንዲሁም የቤተሰብ ትስስር እንዲጠናከር እንደሚረዱ እዝራ ያምናል።

"ልዩነት ቢኖር እንኳን የጋራ የሆነ መስማሚያ ቦታ፣ ቋሚ ድልድይ መፍጠር አስፈላጊ ይመስለኛል። ሥነ ጥበብ ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚከናወነውን ነገር መልሶ ለማኅበረሰቡ ስለሚያሳይ ይህ ሀሳብ በፌስቲቫሉ ላይ ይገለጻል" ይላል።

ፌስቲቫሉ ዓለም በቪደዮ ሥነ ጥበብ የደረሰበትን ለኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ማስተዋወቅ የሚቻልበት እንደሆነም ይናገራል።

አዲስ የቪድዮ ሥነ ጥበብ ፌስቲቫል ባለፉት ዓመታት ጠጅ ቤት፣ እንደ ቸርችል ባሉ አውራ ጎዳናዎች ላይ፣ እንደ ኤድና ሞል ባሉ መገበያያ ህንጻዎች አቅራቢያ እንዲሁም መርካቶን በመሰሉ ገበያዎች ውስጥም ተካሂዶ ነበር።

ይህም ሥነ ጥበብን ለሕዝቡ ቅርብ እንደሚያደርገው እዝራ ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የኢትዮ ኤርትራ ድንበር በተከፈተበት ጊዜ በደስታ የሚያነቡ እናት

እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም ቪድዮዎችን መንገድ ላይና በሌሎችም ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች የማሳየት እቅድ ቢኖርም፤ ፍቃድ ስላላገኙ ፌስቲቫሉ በሥነ ጥበብ ጋለሪዎችና በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት እንደሚካሄድ ገልጾልናል።

ዛሬ ምሽት በገብረ ክርስቶስ ደስታ የሥነ ጥበብ ማዕከል ተከፍቶ፤ ሰባት ቀን የሚቆየው ፌስቲቫሉ፤ ታህሳስ 22፣ 2012 ዓ. ም. በጅማ ጠጅ ቤት ጋቢ ወጥሮ ቪድዮ በማሳየት እንደሚገባደድ እዝራ ነግሮናል።