በፊሊፒንስ የተፈጥሮ አደጋ ቢያንስ 10 ሰዎች ሞቱ

በጎርፍ የተጠልቀለቀ መንገድ ላይ የሚራመዱ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ፊሊፒንሳውያን የገና በአልን በማክበር ላይ እያሉ በጣለ ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ 10 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ የሟቾች ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ተሰግቷል።

'ታይፉን ፋንፎን' ወይንም 'አርስላ' በመባል የተጠራው ክስተት በሰዓት 180 ኪሎሜትር የሚምዘገዘግ ንፋስና ከባድ ዝናብን ይዞ ነበር ፊሊፒንስ ደረሰው። ወዲያውም ከፍተኛ ጎርፍንና የመሬት መንሸራተት አስከትሏል።

የገና በአልን ተሰብስበው ሲያከብሩ የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ወደቤታቸው መመለስ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ይሄው ተመሳሳይ የተፈጥሮ ክስተት በአውሮፓውያኑ 2103 በፊሊፒንስ ተከስቶ ከስድስት ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በሀገሪቱ ታሪክ እጅግ አስከፊው አደጋ ተብሎ ነበር።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ቢያንስ 10 ሰዎች በትናንቱ አደጋ ህይወታቸው ሲያልፍ ከሟቾች መካከል አንድ የሶስት ዓመት ህጻን ይገኝበታል። አብዛኛዎቹ ሰዎች የሞቱት ኢሊሎ እና ካፒዝ በሚባሉት ግዛቶች እንደሆነም ተዘግቧል።

የፈረንሳዩ የዜና አውታር አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ግን የሟቾች ቁጥር በትንሹ 16 እንደሆነ ዘግቧል።

የፊሊፒንሱ 'ኤቢኤስ-ሲቢኤን' የተባለው የዜና ወኪል በበኩሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት ወደከፍታ ቦታ ለመሄድ ጥረት በማድረግ ላይ ሳሉ በጎርፍ ተወስደዋል ሲል ዘግቧል። ቢያንስ 12 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በህይወት ይኑሩ አይኑሩ የታወቀ ነገር የለም ሲል አክሏል።

የሀገሪቱ የአየር ጸባይ ቅድመ ትንበያ መስሪያ ቤት ደግሞ 'ታይፉን ፋንፎን' ከረቡዕ ምሽት ጀምሮ በፊሊፒንስ ሰማይ ላይ ሲያንዣብብ መቆየቱን ጠቅሶ አሁን ወደ ደቡብ ቻይና ባህር ማቅናቱን አስረድቷል።