የኤርትራና ኳታር ቅራኔ

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂና የኳታሩ ኢምር ሼኽ ታሚም ቢን ሐማድ አልታኒ

ኤርትራ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከባሕረ ሰላጤው አረብ አገራት ጋር ለዓመታት የተገነባ ጥብቅ ግንኙነት አላት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቀደም ሲል ወዳጇ ከነበረችው ኳታር ጋር ያላት ግንኙነት ከመቀዛቀዝ አልፎ በግልጽ እስከ መካሰስ ደርሷል።

የኤርትራ መንግሥት ከኳታር ጋር የመረረ ውዝግብና ክስ ውስጥ ገብቶ ባለፉት ወራት ብቻ ኳታር የኤርትራን መንግሥት ለማዳከም የተለያዩ ጥረቶችን እንዳደረገች የሚገልጹ ጠንካራ ክሶች ስታቀርብ ኳታር ግን በተደጋጋሚ ስታስተባብል ቆይታለች።

ኤርትራ ቅሬታዋን ስታቀርብ የቆየችው በኳታር ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት የኤርትራ መንግሥት ያወጣቸው ክሶች ሱዳንና ቱርክንም የሚጨምሩ ናቸው። ከእነዚህም በአንዱ ኳታር በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ግንኙነት ደስተኛ አይደለችም ሲል ጎንተል አድርጓታል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ በኤርትራ መንግሥት የወጣው መግለጫ ሦስቱንም አገራት ያካተተ ነበር። በዚህም ኳታርና ሱዳን ያቀናጁትን "አፍራሽ" ተግባር በኅብረት እየሰሩ እንደሆነና፤ ቱርክም ተሳታፊ በመሆን የአገራቱ "ጥንስስ እያማሰለች" እንደሆነ ይጠቅሳል።

በተለይም ቱርክ ሱዳንን ማዕከሉ ያደረገውን የሙስሊም ምክር ቤትን [መጅሊስ ሹራ ራቢጣ ኡላማአ ኤሪትሪያ] በመደገፍ፤ ኤርትራን ለማወክ እየሰራች መሆኑንና ሱዳንም ተባባሪ እንደሆነች መክሰሱ ይታወሳል።

ባለፈው ወር የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው ጠንከር ያለ መግለጫ ደግሞ፤ "ኳታርና ሸሪኮቿ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎችንና የፖለቲካ መሪዎች እንዲሁም ወጣቶችን በመቀስቀስ የጦር መሳሪያ እንዲታጠቁና ተቃውሞ እንዲያስነሱ ተዘጋጅታለች" ሲል ከሷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂ

ይህ ክስ "ውሸት ነው" ብላ ያጥላላችው ኳታር በበኩሏ፤ ኤርትራ ውስጥ ካሉ ቡድኖች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላት አመልክታ፤ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኳታር የኤርትራ አምባሳደርን በመጥራት አገራቸው ለኤርትራ ክስ ያላትን "ተቃውሞ" የሚገልጽ ሰነድ ሰጥተዋል።

ኤርትራና ኳታር የሁለትዮሽ ግኑኝነት ነበራቸው?

በአንድ ወቅት፤ የኤርትራው ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ኳታር አዘውትረው ከሚጎበኟቸው አገራት መካከል ቀዳሚዋ ነበረች። የሁለቱ መንግሥታት ወዳጅነትም ጠንካራና እንደነበረም፤ የቀጠናውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ይናገራሉ።

ለዚህም ከ10 ዓመታት በፊት በድንበር ይገባኛል ምክንያት ግጭትና ውዝግብ ውስጥ ገብተው የነበሩት ኤርትራና ጂቡቲን ለማስማማት ጥረት ከማድረግ አልፋ በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ ሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን እስከማስፈር ደርሳ ነበር። ይህም ኳታር ከኤርትራ ጋር ለነበራት ወዳጅነት እንደ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊነሳ ይችላል።

ኤርትራ፤ በሱዳንና በኳታር ላይ ክስ ማቅረብ ከመጀመርዋ በፊትም፤ "የቤጃ እርቅ" ተብሎ የሚጠራውንና በምሥራቅ ሱዳን የነበረውን ችግር ለመፍታት የተደረገው ስምምነት አገሯ ላይ እንዲፈረም አድርጋለች።

ለዚህም በወቅቱ የኤርትራ የቅርብ ወዳጅ የነበረችው የኳታር ድጋፍ እንደነበረት የአፍሪካን ፕሮግረስ ሴንተር ኃላፊና የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ዓሊ ህንዲ ለቢቢሲ ይገልጻሉ።

የኋላ የኋላ ግን ወዳጅነታቸው የሚያሻክር ክስተት መከሰቱን ጨምረው ይጠቅሳሉ፤ ኳታር በመካከለኛው ምሥራቅና በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ኃያል ከሆኑት ከሳኡዲና ከኤምሬትስ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ስትገባ ጂቡቲና ኤርትራ ኳታርን ገሸሽ አድርገው ወዳጅነታቸውን ከሁለቱ አገራት ጋር አጠናከሩ። ኳታርም ወታደሮቿን አስወጣች።

የፍጥጫው ጅማሬ

የመካከለኛው ምሥራቅና የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንተኝ የሆኑት አቶ ዓብዱልራሕማድ ሰይድ አቡሃሽም፤ ለዚህ መነሻ የሆነውን ምክንያት ሲጠቅሱ፤ በገልፍ አረብ የሚገኙት ኤሜሬትስና ሳውዲ ኳታርን የሚቃወም አቋም በመውሰድ የየብስና የባሕር ማዕቀብ መጣላቸው ነው።

ኤርትራም ከኳታር ጋር የነበራት ግንኙነት በማቋረጥ የሳኡዲና የኤምሬትስን ጎራ በመቀላቀል፤ አገራቱ በመን አማጺያን ላይ የሚያካሂዱትን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ደግፋ ቆመች። ይህም ኤርትራ ወዳጇ የነበረችውን ኳታርን ትታ በሳኡዲ ከሚመራው ጥምረት ጋር በመቆሟ የሁለቱ አገራት ግንኙነትም ሌላ መልክ ወደ መያዝ አመራ።

"የኤርትራ መንግሥት ወደዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ኤምሬቶች አሰብ ውስጥ ወታደራዊ ካምፕ ስላላት ነው። በተጨማሪም ሥርዓቱ ከሁለቱ አገራት የተለያዩ ድጋፎችን ያገኛል። ስለዚህ ከኳታር ጋር ለነበረው ግንኙነት መሻከር መነሻው የኤርትራ መንግሥት ኳታርን ማንበርከክ ከሚሹ ኃይሎች ጋር በመሰለፉ ነው" ይላሉ አቶ ዓብዱልራሕማድ።

በመካከለኛው ምሥራቅና በባሕረ ሰላጤው አካባቢ በሚገኙ አገራት መካከል ላለው ፍጥቻ መባባስ በሳኡዲ የሚመራው ጥምረት በመን ላይ የሚያካሂደው ዘመቻ ምክንያት ሆኗል።

ኳታር ዘመቻውን በመቃወሟ የተለያዩ ክሶች የቀረቡባት ሲሆን በተጨማሪም ለአካባቢው አገራት መንግሥታት ስልጣን ስጋት የሆነውን 'ሙስሊም ብራዘርሁድ' እንቅስቃሴን ትደግፋለች ብለውም ይወንጅሏታል።

ኳታር በመካከለኛው ምሥራቅ ኃያል አገራት መገለል ሲደርስባትና ሌሎችም ከእነሱ ጎን ሲቆሙ ብቻዋን ግን አልቀረችም። ቱርክ ኳታርን በመደገፍ በአካባቢው ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ሚና አጠናክራለች ይባላል።

ለ30 ዓመታት ሱዳንን ያስተዳደሩት ኦማር አልበሽር ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት፤ ኤርትራና ሱዳን አልፎ አልፎ አለመግባባት ይገጥማቸው ነበር። ነገር ግን አልበሽር በተቃውሞ ከሥልጣናቸው ከተነሱ በኋላ የሁለቱንም አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በካርቱምና አስመራ ሲገናኙ ታይተዋል።

"ሱዳኖች የራሳቸው የውስጥ ችግሮች ስላሉባቸው በዚህ ጊዜ ከኳታር ጋር በማበር ኤርትራን ለማጥቃት ፍላጎት አይኖራቸውም። በእኔ አስተያየት ሱዳን በሌላ አገር ላይ አዲስ ችግር ለመፍጠርና ራሷን ውዝግብ ውስጥ ለመክተት አትፈልግም" ይላሉ አቶ አብዱልራሕማድ አቡሃሽም።

ኳታር የሳኡዲና ኤምሬቶችን ተጽእኖ ለመመከት በምሥራቅ አፍሪካ እንቅስቃሴ እንደነበራት የሚያነሱት የአፍሪካን ፕሮግረስ ሴንተር ሃላፊና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ዓሊ ህንዲ በበኩላቸው፤ የሙሰሊም ክንፍ የሆነው 'ሙስሊም ብራዘርሁድ' በመደገፍ አቅሟን ለማጠናከር ብዙ አማራጮች ትጠቀም እንደነበር ይገልጻሉ።

ኳታር ቀደም ሲል ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ነበራት፤ ነገር ግን በአረቡ ዓለም የተቀሰቀሰውን አብዮት ተከትሎ 'ሙስሊም ብራዘርሁድ' በግብጽ ሥልጣን በያዘበት ጊዜ ከኤርትራ የሙስሊም ቡድኖች ጋር ግንኙነት ጀምሯል የሚሉ መረጃዎች ሲሰሙ፤ በወቅቱ ኤርትራ ደስተኛ አለመሆንዋ መግለጽዋን ያስታውሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም "የፎርቶ ኦፕሬሽን በሚባለውና የኤርትራ የሠራዊት አባላት በታንክ ታጅበው ወደ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በመሄድ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ለማንሳት ያደረጉት ሙከራ ላይ የኳታር እጅ አለበት ተብሎ ስሟ ሲነሳ ነበር። በእነዚህ ምክንያቶች ጠንካራና እውነተኛ ሲባል የነበረው ግንኙነታቸው ወደ ጥላቻ አመራ" ይላሉ አቶ አሊ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የኳታሩ ኢምር ሼኽ ታሚም ቢን ሐማድ አልታኒ

ኤርትራ ከነጻነት ትግሉ ጊዜ አንስቶ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ጋር ቅርብ የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር ችላለች። ከኳታርም ጋር ያላት ግንኙነት ከዚሁ አንጻር የሚታይ ቢሆንም በመካከላቸው ንፋስ ከመግባቱ ቀደም ብሎ ጠንከር ያለ ነበር።

ለዚህም ይሆናል ኤርትራ በአረቡ ዓለም ካሏት ኤምባሲዎች ሁሉ ኳታር ውስጥ የሚገኘው ትልቁ የሆነው።

የኤርትራ መንግሥትም የአገራቱን ፖለቲካና ፍላጎት በቅርበት ስለሚያውቀው ከቀጠናው አገራት ጋር ምን አይነት ግንኙነት እንደሚኖረውና ብሔራዊ ጥቅሞቹን እንዴት ማስጠበቅ እንዳለበት በቀላሉ የመረዳት ልምድ እንዳለው አቶ ዓሊ ይገልጻሉ።

ኤርትራ በቅርቡ ያወጣቻቸው ኳታርን የሚከስ መግለጫ፤ የተለያዩ ድጋፎችን ለኤርትራ በምትሰጠው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና አጋሮቿ የተገፋ ሊሆን እንደሚችል አቶ አብዱልራሕማን አቡሃሽም ይናገራሉ።

በሳኡዲ የሚመራው ጥምረትና ኳታር በመካከላቸው ያለው መቃቃር በዚህ ከቀጠለ ለኤርትራ መንግሥት መልካም አጋጣሚን ይፈጥርለታል የሚሉት አቶ አሊ፤ የኤርትራ መንግሥት አሁን ካለው ሁኔታ ተቃዋሚ መሆኑን በማመልከትም "ምናልባት ኳታር ከእነዚህ አገራት ጋር እርቅ ካወረደች ግን ሌላ መንገድ ለመፈለግ ይገደዳል" ይላሉ።

የፖለቲካ ተንታኙ አብዱልራሕማን ሰይድ በበኩላቸው፤ ይህ በአፍሪካ ቀንድ አገራትና በባሕረ ሰላጤው መንግሥታት መካከል ያለው ፖለቲካ ለቀጠናው ትልቅ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ያምናሉ።