ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ሰምጣ 7 ሰዎች ሞቱ

የቱርክ የድንበር ጠባቂዎች በጀልባ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በምሥራቃዊ ቱርክ በሚገኘው ቫን በተባለ ሐይቅ ላይ ከፓኪስታን፣ ከባንግላዲሽና ከአፍጋኒስታን የመጡ ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ሰምጣ ቢያንስ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ።

ሐይቁ ቱርክን ከኢራን ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ የሚገኝ ሲሆን በርካታ ወደ አውሮፓ ለማቅናት የሚፈልጉ ስደተኞች የሚያልፉበት ነው ተብሏል።

ከአደጋው 64 ሰዎች በነፍስ አድን ሠራተኞች አማካይነት የተረፉ ሲሆን ወደ ሆስፒታልና ወደ መጠለያ ማዕከላት መወሰዳቸውም ተገልጿል።

የአካባቢው ባለስልጣናት እንደተናገሩት ስደተኞቹ የነበሩባት ጀልባ ወደ ሐይቁ ሰሜናዊ ዳርቻ እየተቃረበችበት በነበረ ጊዜ ነው የመገልበጥ አደጋ የደረሰባት።

ከአደጋው በኋላ በቦታው አምስት ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፎ የተገኙ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ሆስፒታል ውስጥ መሞታቸው ተነግሯል።

በአገራቸው የሚደርስባቸውን ጥቃትና ማሳደድ ለማምለጥ የሚጥሩ ሰዎች ወደ አውሮፓ ለመሸሽ ብዙ ጊዜ በቱርክ በኩል የሚያቋርጡ ሲሆን ብዙዎቹ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን በመከተል አደገኛ የባሕር ላይ ጉዞዎችን ያደርጋሉ።

የቱርክ መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው አናዶሉ እንደዘገበው የአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ካለ ሕጋዊ ሰነድ የተገኙ ከ440 ሺህ በላይ ስደተኞችን ይዘዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት ቱርክ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ስደተኞችን ለመቆጣጠር ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የገንዘብ ስምምነት ደርሳ ነበር። በኅዳር ወር ላይ አንድ የአውሮፓ ሕብረትን ምስጢራዊ ሪፖርት ጠቅሰው የጀርመን መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት አብዛኞቹ ከአፍጋኒስታን የሆኑ በቱርክ በኩል የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው።

ቱርክ በአሁኑ ጊዜ በምድራችን ከፍተኛ የተባለውን የስደተኞች ቁጥር እንደምታስተናግድ የተነገረ ሲሆን፤ እነሱም 3.7 ሚሊዮን የሚደርሱ ሶሪያዊያን ናቸው ተብሏል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ሶሪያዊያን ስደተኞች በአዲስ አበባ