"ተንሰራፍቶ የነበረው ሙስና ለመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ አንድ ምክንያት ነው"- የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር

የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም

የፎቶው ባለመብት, Fana Broadcasting Facebook page

በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የሙስና ወንጀል መጠን እየጨምረና ወንጀሉ የሚፈጸምበት ረቂቅነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቀ መምጣቱ ተነገረ።

የኢትዮጵያ የሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሙስና ወንጀል በአገር ላይ እያስከተለ ያለውን ኪሳራ ለመከላከል የተደራጀ እና ንቃተ ህሊናው ከፍ ያለ ማኅብረሰብ ለመፍጠር እንዲሁም ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ፤ የሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ፖሊስ እንዲሁም አቃቤ ሕግ በጥምረት ከመቼውም በላይ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ከለውጡ ጋር ተያይዞ የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ከመቼውም በላይ የተነቃቃበት እና የተለወጠበት ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ እርሳቸው የሚመሩት ኮሚሽን ግን ከዚህ ቀደም የነበረውን አይነት ተጽእኖ መፍጠር እንደማይችል ይስማማሉ።

የኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም የነበሩት ኃላፊነቶች እንዲቀሩ መደረጉ የነበረውን ተደማጭነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነትን እንዳሳጣው ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከፖሊስ እና ከአቃቢ ሕግ ጋር በቅርበት ስለሚሰራ እንደተቋም ተዳክሟል ማለት አይቻልም የሚሉት ኮሚሽነር አየልኝ፤ "ወደፊት ግን ሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ተብሎ እስከተቋቋመ ድረስ ያለ ምርመራ ጠንካራ ሆኖ ለኅብረተሰቡ ችግር ምላሽ መስጠት የሚችል አይሆንም" ብለዋል።

ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቀደም ሲል ሙስናን የመከላከል፣ የሙስና ወንጀል የመመርመርና ሕግ የማስከበር ኃላፊነቶች እንደነበሩት አስታውሰው፤ አሁን ግን ለሙሰና ተጋላጭ የሚያደርጉ አሰራሮችን ማሻሻል፣ ተቋማትን ማጠናከር እና መደገፍ፣ እንዲሁም ሙስናን የሚጠየፍ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ጸረ-ሙስናን የሚያጠናክር እና አቅም እንዲኖረው የሚያስችል አሠራር ቢዘረጋ መልካም ነው የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ "ሙስና የሚፈጸምባቸው የወንጀል አይነቶች እየተራቀቁ እንደመምጣታቸው ወንጀሉን የመከላከል እና የመመርመር ሥራው ተጣምሮ አቅሙ ባላቸው ብቁ ሠራተኞች ቢከናወን ውጤታማ መሆን ይቻላል" ሲሉም ይጠቁማሉ።

ኮሚሽነሩ 2007 እና 2008 አካባቢ ኮንትሮባንድን ጨምሮ በኢትዮጵያ በተደራጀ መልኩ ሕገ-ወጥ ንግድ የተስፋፋበት ዓመት እንደነበረ ይናገራሉ።

"የመንግሥት ሃብት እና ንብረት በተደራጁ ኃይሎች ምዝበራ የተካሄደበት፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ሰዓት ካለመጠናቀቃቸው ባሻገር ተጨማሪ ሃብት እንዲወጣባቸው የተደረገበት፣ ጨረታ ከግልጽ አሰራርነት ይልቅ በትውውቅ ሲከናወኑ የቆዩባቸው ዓመታት ነበሩ" የሚሉት ኮሚሽነር አየልኝ፤ ይህ የተንሰራፋው የሙስና ወንጀል ህዝቡን አስመርሮ በኢትዮጵያ የታየውን አይነት የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ይናገራሉ።

ኮሚሽነር አየልኝ፤ የመንግሥት ባለስልጣናትን ሃብት እና ንብረት የመመዝገቡ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱ ሲሆን፤ ከወረዳ ጀምሮ እሰከ የፌደራል ክፍተኛ ባለስልጣናት የሚገኙ የ180 ሺህ ግለሰቦች በላይ ሃብትና ንብረት እንደተመዘገበ ይናገራሉ።

ኮሚሽነር አየልኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ሆኑ ሌሎች ባለስልጣናት ሀብታቸውን ቀደም ሲሉ ቢያስመዘግቡም በወቅቱ የማሳደስ ክፍተት መኖሩን ግን ያስረዳሉ።

አንድ የመንግሥት ሠራተኛም ሆነ ባለስልጣን ሀብቱን ካስመዘገበ በኋላ በየሁለት ዓመቱ ማሳደስ እንደሚኖርበት ያስታወሱት ኮሚሽነሩ ነገር ግን የእድሳት ዘመኑን ጠብቆ ማሳደስ ላይ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም እስካሁን ባለው ልምድ እድሳቱን ማከናወንና የግለሰቦችን ንብረት ትክክለኛነት የማረጋገጥ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጨምረው ተናግረዋል።