በፊሊፒንስ በከባድ አውሎ ንፋስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 28 ደረሰ

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በአውሎ ንፋሱ ምክንያት የሞቱና የተጎዱ ሰዎችን እየሰበሰቡ ነው። ከተጎዱና ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ የአሳ አጥማጆች ናቸው ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፊሊፒናዊያን የገና በአልን በማክበር ላይ እያሉ በጣለ ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 28 መድረሱ ተገለጸ።

'ታይፉን ፋንፎን' ወይንም በአካባቢው ሰዎች አጠራር 'አርስላ' በመባል የሚታወቀው አውሎንፋስ በሰዓት 180 ኪሎሜትር የሚምዘገዘግ ንፋስና ከባድ ዝናብን ይዞ ነበር ፊሊፒንስ የደረሰው። ወዲያውም ከፍተኛ ጎርፍንና የመሬት መንሸራተት አስከትሏል።

እንደ ሀገሪቱ ብሔራዊ አደጋ መከላከልና መቀነስ ካውንስል ከሆነ አሁንም 12 ሰዎች እምጥ ይግቡ ስምጥ አልታወቀም።

በታይፋን ፋንፎን አውሎ ንፋስ ምክንያት 58ሺህ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ለቅቀው ሲሄዱ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መንቀሳቀሻ አጥተው ታግተው ይገኛሉ።

እንደባለስልጣናት ገለፃ የሞቱት ሰዎች አንዳንዶቹ ዛፍ ሌሎቹ ደግሞ የኤሌትሪክ መስመር ወድቆባቸው ነው።

ፋንፎን በዚህ ዓመት ፊሊፒንስን ከመቷት ሰባት አውሎ ነፋሳት አንዱ ነው።

ይሄው ተመሳሳይ የተፈጥሮ ክስተት በአውሮፓውያኑ 2103 በፊሊፒንስ ተከስቶ ከስድስት ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በሀገሪቱ ታሪክ እጅግ አስከፊው አደጋ ተብሎ ነበር።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት አብዛኛዎቹ ሰዎች የሞቱት ኢሊሎ እና ካፒዝ በሚባሉት ግዛቶች ነው።

ራፕለር የተሰኘ መገናኛ ብዙኀን እንደዘገበው ከሆነ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለቀብር የሄዱ ስድስት የቤተሰብ አባላት በአውሎ ንፋሱ ምክንያት ሞተዋል።

የቱሪስት መናኸሪያ የሆነችው ቦራኬይ በአውሎንፋሱ የወደመች ሲሆን የስልክ መስመርም ሆነ የኤሌትሪክ ኃይል ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል ሲል የፈረንሳዩ ዜና ወኪል የአቅራቢያዋን ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ጠቅሶ ዘግቧል።

የሀገሪቱ የአየር ጸባይ ቅድመ ትንበያ መስሪያ ቤት ደግሞ 'ታይፉን ፋንፎን' ከረቡዕ ምሽት ጀምሮ በፊሊፒንስ ሰማይ ላይ ሲያንዣብብ መቆየቱን ጠቅሶ አሁን ወደ ደቡብ ቻይና ባህር ማቅናቱን አስረድቷል።