ካዛክስታን ውስጥ የመንገደኞች አውሮፕላን ተከሰከሰ

አደጋው የደረሰበት አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዘጠና ስምንት ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ የካዛክስታን አውሮፕላን ወድቆ በመከስከሱን ቢያንስ 14 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ አየር ማረፊያ ባለስልጣናት ተናገሩ።

በአደጋው ቢያንስ 35 ሰዎች የመቁደሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከእነሱም መካከል ስምንቱ ህጻናት መሆናቸውን የአካባቢው የሆስፒታል ምንጮች ገልጸዋል።

ባለስልጣናቱ እንዳሉት ቤክ ኤር የተባለ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ከአልማቲ አየር ማረፊያ ዛሬ ጠዋት ከተነሳ ከአጭር ጊዜ በኋላ ነበር የወደቀው።

በመጀመሪያ ላይ በአስቸኳይ ወደ ስፍራው የደረሱት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሰባት ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠው ነበር፤ ነገር ግን የሟቾቹ ቁጥር ወደ 14 ከፍ ብሏል።

አደጋው ከደረሰበት ስፍራ አቅራቢያ የነበረ ቨየሮይተርስ ዘጋቢ እንዳለው በአካባቢው ከባድ ጭጋግ እንደነበረ ያመለከተ ቢሆንም የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።

አውሮፕላኑ ከካዛክስታኗ ትልቅ ከተማ አልማቲ ተነስቶ ወደ ዋና ከተማዋ ኑር-ሱልጣን ለመጓዝ ነበር መንገደኞችን ይዞ የተነሳው።

የአውሮፕላን ማረፊያው ባለስልጣናት እንዳሉት በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት 93 መንገደኞች ሲሆኑ 5ቱ ደግሞ የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ነበሩ።

አክለውም አውሮፕላኑ እንደተነሳ ከቁጥጥር ውጪ መሆኑንና መጀመሪያ ላይ የመከለያ ግንብ ገጭቶ ከባለ ሁለት ፎቅ ህንጻ ጋር ተጋጭቶ ነው የወደቀው።

ነገር ግን አደጋው ከደረሰ በኋላ በአውሮፕላኑ ላይ እሳት አላጋጠመም ነበር።

የአደጋውን ምክንያት ለማጣራት ልዩ ኮሚሽን እንደሚቋቋምም ተነግሯል።

የካዛክስታን ፕሬዝዳንት ቃሲም-ጆማርት ቶቃዬቭ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች "ጥልቅ ሐዘናቸውን" ገልጸዋል።

ይህ አደጋ በአልማቲ ውስጥ ያጋጠመ የመጀመሪያው የከፋ አደጋ አይደለም እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2013 ላይ ከሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የተነሳ አውሮፕላን በከተማዋ አቅራቢያ ተከስክሶ የ20 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል።

ከዚህ አደጋ አንድ ወር ቀደም ብሎ ደግሞ የካዛክስታን ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣናትን ያሳፈረ ወታደራዊ አውሮፕላን በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ተከስክሶ ለ27 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኖ ነበር።