አይኤስ ናይጄሪያ ውስጥ አስራ አንድ ታጋቾችን ገደለ

ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአይኤስ ቡድን ይዟቸው የነበሩ 11 ክርስቲያኖችን መግደሉን የሚያሳይ ቪዲዮ ለቀቀ።

ቡድኑ እንዳለው ይህ እርምጃ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ሶሪያ ውስጥ ተገደሉትን መሪውንና ቃል አቀባዩን ደም "ለመበቀል" ያወጀው ዘመቻ አካል ነው።

የአይኤስ ግድያ ሰለባ ሆነዋል የተባሉት ታጋቾች በሙሉ ወንዶች ሲሆኑ ስለማንነታቸው ምንም አይነት ዝርዝር አልሰጠም።

ነገር ግን ቡድኑ እንዳለው ሰዎቹ ሰሜናዊ ናይጄሪያ ውስጥ በምትገኘው የቦርኖ ግዛት "ባለፈው ሳምንት የተያዙ" መሆናቸው ተጠቅሷል።

ይህ በተያዙት ሰዎች ላይ ስለተወሰደው እርምጃ የተለቀቀው ቪዲዮ የ56 ሰከንዶች ርዝመት ያለው ሲሆን የተዘጋጀውም አማቅ በተባለው የአይኤስ "የዜና ወኪል" ነው።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ የተለቀቀው ትናንት ሲሆን ተንታኞች ጊዜው የተመረጠው ከፈረንጆቹ የገና በዓል ጋር እንዲገጥም ሆን ተብሎ እንደሆነ ግልጽ ነው ብለዋል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ የተቀረጸው በውል ባልተገለጸ ቦታ ከቤት ውጪ ነው ተብሏል።

በቪዲዮው ላይ ከተያዙት ሰዎች መካከል አንዱ በጥይት ሲረሸን ቀሪዎቹ ግን መሬት ላይ ሆነው አንገታቸው ሲቀላ ያሳያል።

የአይኤስ የቀድሞ መሪ አቡ ባክር አልባግዳዲና ቃል አቀባዩ አቡ ሀሳን አል ሙሃጂር ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ሶሪያ ውስጥ ነበር የተገደሉት።

ከሁለት ወራት በኋላም አይኤስ የሁለቱን ሞት ለመበቀል አዲስ ወታደራዊ ዘመቻን ጀምሮ በተለያዩ አገራት ውስጥም ተከታታይ ጥቃት እንደፈጸመ ጠቅሷል።

ናይጄሪያ ውስጥ የሚገኘው እስላማዊ ቡድን የቦኮ ሃራም አንድ አንጃ "በምዕራብ አፍሪካ የእስላማዊ መንግሥት" በሚል ስያሜ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ባለፈው ዓመትም ቡድኑ ይዟቸው የነበሩ ሁለት ነርሶችን ገድሏል።