የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የፓርቲያቸውን ምርጫ አሸነፉ

ናታንያሁና ጌዲዮን Image copyright AFP/EPA
አጭር የምስል መግለጫ የናታንያሁ ተፎካካሪ ግዲዮን ሽንፈታቸውን አምነዋል

ከዛሬ ነገ ዘብጥያ ይወርዳሉ ሲባሉ የነበሩት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በከፍተኛ ድምጽ የፓርቲያቸውን ሊቀመንበርነት ማሸነፋቸውን እየተናገሩ ነው።

ያሸነፍኩትም በከፍተኛ ልዩነት ነው ብለዋል።

ሊኩድ ፓርቲ ውስጥ በመሪነት ለመቀጠል ከተወዳዳሪያቸው ጌዲዮን ሳር ከፍተኛ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።

ድምጽ መስጠት ከሚችሉት 116 ሺህ የፓርቲው አባላት ውስጥ 49 ከመቶ የሚሆኑት ለእኔ ድምጻቸውን ሰጥተዋል ብለዋል ናታንያሁ።

ተፎካካሪያቸው ጌዲዮን ሳር ሽንፈቴን ተቀብያለሁ፤ ከዚህ በኋላ ከናታንያሁ ጎን እቆማለሁ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

"ሙስና ለመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ አንድ ምክንያት ነው"

ሞሳድ ቤተ-እስራኤላዊያንን ለመታደግ የፈጠረው ሐሳዊ ሪዞርት

ሦስት የሙስና ክሶች ለተከመሩባቸው ናታንያሁ ይህ ድል ትልቅ ስኬት እንደሆነ የፖለቲካ አዋቂዎች ይናገራሉ።

የ70 ዓመቱ ናታንያሁ በአንድ ዓመት ውስጥ የሙስናና የማጭበርበር ክሶችን ይፋለማሉ፣ አዲስ ምርጫም ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

በአንድ ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ምርጫ የሚካሄድባት እስራኤል ባለፈው መስከረም ናታንያሁም ሆነ ቤኔ ጋዝ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችላቸውን መቀመጫ ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

የሽርክና መንግሥት ለመመሥረትም ማን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል በሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት መድረስ አልቻሉም።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ናታንያሁ እና ቤን የጥምር መንግሥት አልተሳካላቸውም

ባለፈው ሚያዚያ እና መስከረም በተካሄዱ ምርጫዎች ሊኩድ ፓርቲ 33 ወንበሮችን ካሸነፈው የብሉና ዋይት ፓርቲ ጋር የጥምር መንግሥት ለመመሥረት ሳይቻለው ቀርቷል።

ናታንያሁ አሸነፍኩ የሚሉት የፓርቲያቸው መሪነት ይፋዊ ውጤት ዛሬ [አርብ] አመሻሹን የሚጠበቅ ቢሆንም እርሳቸው ግን ከወዲሁ አትጠራጠሩ ድል ቀንቶኛል ብለዋል።

"በፈጣሪና በእናንነት እርዳታ ሊኩድ ፓርቲን በድጋሚ ለመምራት ተመርጫለሁ። በመጪው አገራዊ ምርጫም ለትልቅ ድል ተሰናድቻለሁ። ድሉ ይቀጥላል" ብለዋል፤ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ በሂብሩ ቋንቋ ባሰፈሩት የድል ብስራት።

ጌዲዮን በበኩላቸው በመጪው አገራዊ ምርጫ ከናታንያሁ ጎን እቆማለሁ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ፅዮን ውሰዱን ተማፅኖ

"ኢትዮጵያዊነቴን ያገኘሁት ሙዚቃ ውስጥ ነው" አቨቫ ደሴ

ሐሙስ በነበረበው አስቸጋሪ የአየር ንብረት በርካታ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ዳተኛ ነበሩ። ናታንያሁ ግን በፌስቡክ ላይቭ በመምጣት ሰዎች ወጥተው ድምጽ እንዲሰጡ አበረታተዋል።

ባለፈው ወር ናታንያሁ ሦስት የሙስና ወንጀሎች ቀርበውባቸዋል። እርሳቸው ግን ንጹህ ነኝ፤ ክሱ እኔን ከፖለቲካ ለማግለል የተቀነባበረ ተራ ሴራ ነው ይላሉ።

ቤንያሚን ናታንያሁ በእስራኤል ታሪክ ረዥም ጊዜ በሥልጣን የቆዩ መሪ ናቸው።