በመስጅዶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሄዱ

ወልዲያ

የፎቶው ባለመብት, AMMA/FB

በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በመስጅዶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄዱ።

ባሳለፍነው ሳምንት በሞጣ ከተማ በአራት መስጅዶች ላይ የደረሰውን ጥቃት ለማውገዝ ከተደረጉት ሰልፎች አብዛኛዎቹ የተካሄዱት በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች ነው።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እውቅና አልሰጠሁትም ያለው የተቃውሞ ሰልፍ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል አዲስ አበባ፣ ሀዋሳ፣ አሰላ፣ ጅማ፣ ደሴ፣ መርሳ፣ ወልዲያ፣ ባሌ እና በደሌ ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው።

በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች እንዲበተን መደረጉን በስፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን ዘግቧል።

በአማራ ክልል የተደረጉት ሰልፎች በሰላም መጠናቀቃቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ አስታውቋል።

በምሥራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ አራት መስጅዶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ 27 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, AMMA/FB

ለተቃውሞ ሰለፍ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች "የኃይማኖት ተቋማት መቃጠል መንግሥት የሚያሳየውን ቸልተኝነት ያሳያል"፣ "ለሁሉም የእምነት ተቋማት ጥበቃ ይደረግላቸው" እንዲሁም "ሚዲያዎች ያለ አድልዎ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ይዘግቡ" የሚሉ መፈክሮችን ይዘዋል።

በደሴ ከተማ የተካሄደውን ሰልፍ ሲያስተባበሩ ከነበሩት መካከል አቶ ከማል ሁሴን አንዱ ናቸው።

አቶ ከማል "ይህ ድንገተኛ ጥቃት አይመስልም። ያን ያክል ቁጥር ያለው ህዝብ እየጨፈረ መስጅድ ሲወድም የሚያስቆም መንግሥት የለም ወይ? ይሄ ሆነ ተብሎ ድንገተኛ አደጋ ለማስመሰል ተሞክሯል። እዚህ ያለው ህዝብ የክልሉ መንግሥትን ጥፋተኛ ያደረገው" ይላሉ።

አቶ ከማል ጨምረውም በጥቃቱ ንብረታቸው ለወደመባቸው ግለሰቦች የክልሉ መንግሥት ካሳ እንዲከፍላቸው መጠየቁን ተናግረዋል።

ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች ሌላኛዋ በደሴ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈችው ወጣት፤ የተካሄደው ሰላማዊ ሰለፍ በሰላም መጠናቀቁን ከተናገረች በኋላ፤ "ጥቃቱ ሲፈጸም መንግሥት ባፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ለምን ተሳነው?" የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው ብላለች።

በሞጣ ከተማ የሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ጭስ መታየቱን ተከትሎ፤ በከተማዋ በሚገኙ አራት መስጅዶች ላይ ጥቃት የተሰነዘረው ከሳምንት በፊት ነበር።