አፕል ገንዘብ ካልከፈለኝ ብሎ ያስፈራራው ታሠረ

አይክላውድ

የፎቶው ባለመብት, BBC/Apple

የአይክላውድ አካውንቶችን (iCloud) ሰብሬ ገብቻለሁ በማለት አፕል ገንዘብ ካልከፈለው መረጃ እንሚያወጣ ያስፈራራው ወጣት በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ነዋሪነቱ ለንደን ከተማ የሆነው የ22 ዓመቱ ከሪም አልባይራክ ወንጀሉን መፈጸሙን አምኗል።

አልባይራክ፤ አፕል 100 ሺህ ዶላር ዋጋ ያለው የአይቲዩንስ ስጦታ ካርድ የማይሰጠው ከሆነ 319 ሚሊዮን አካውንቶችን እንደሚሰርዝ ሲያስፈራራ ነበር።

ይሁን እንጂ አፕል ባካሄደው ምረመራ ወጣቱ የአፕልን ሥርዓት አብሮ እንዳልገባ አረጋግጧል።

ወጣቱ ለአፕል ሴኪዩሪቲ ቡድን ኤሜይል በመጻፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አካውንቶችን ሰብሮ መግባቱን አሳውቆ ነበር።

በዩቲዩብ ገጹ ላይ ቪዲዮ በመጫን የአይክላውድ አካውንቶችን እንዴት ሰብሮ እንደሚገባ አሳይቷል።

የጠየቀው ገንዘብ የማይከፈለው ከሆነ የአካውንቶቹን የይለፍ ቃል እንደሚቀይር እና አካውንቶቹ የያዙትን መረጃ ይፋ እንደሚያወጣ አስፈራርቶ ነበር።

ይህን ማስፈራሪያ ካደረሰ ከሁለት ቀናት በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም የብሔራዊ ወንጀል መከላከል ኤጀንሲ እንዳለው ወጣቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካላት ተሰብረው ይፋ የተደረጉ የኢሜይል አድራሻዎችን እና የይለፍ ቃሎችን ከሰበሰበ በኋላ፤ የይለፍ ቃላቸውን ያልቀየሩ ተጠቃሚዎችን አካውንት ለመክፈት ሞከረ እንጂ የአፕልን ሥርዓት ሰብሮ ለመግባት አልሞከረም።

ወጣቱ ለመርማሪዎች "በኢንተርኔት ላይ አቅም ሲኖርህ ዝነኛ ትሆናለች፤ ሁሉም ያከብርሃል" ብሏል።

ወጣቱ ለፈጸመው ወንጀል በይርጋ የሚቆይ የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶበታል። ወጣቱ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ምንም አይነት ወንጀል የማይፈጽም ከሆነ ነጻ ይሆናል። በወንጀል ተጠርጥሮ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ግን የሁለት ዓመት እስሩ ተፈጻሚ ይደረግበታል።

ከዚህ በተጨማሪም አልባይራክ ለ300 ሰዓታት ያለ ክፍያ እንዲሠራ እና ለስድስት ወራት ደግሞ ከኤሌክትሮኒክስ ጋር ግነኙነት እንዳይኖረው ማዕቀብ ተጥሎበታል።