ኢንጂነር አዜብ ላይ የተመሰረተው ክስ ከ5.1 ቢሊዮን ብር ውል ጋር የተያያዘ ነው

ኢንጂነር አዜብ አስናቀ

በቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በነበሩት ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ላይ ከባድ የሙስና ክስ ተመሰረተባቸው።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ህዝብ ግነኙነት ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ ኢንጂነር አዜብ ላይ የተመሰረተው ክስ ከ5.1 ቢሊዮን ብር ውል ጋር የተያያዘ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚያርፍበትን 123ሺህ ሄክታር በላይ ስፋት የሪዘርቨር ክሊሪንግ እና የባዮማስ ዝግጅት ሥራ፤ ደን የመመንጠር፣ የማጽዳት እና ከግድቡ ስፍራ የማጓጓዝ ሥራን ለማስፈጸም ከኢፌዲሪ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር በብር 5.1 ቢሊዮን ብር የጋራ ውል ስምምነት ፈጽሞ እንደነበረ አቶ ዝናቡ ይናገራሉ።

ይህ የስምምነት ውል በተገባበት የስምምነት ጊዜ እና ሂደት ባለመፈጸሙ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱን አቶ ዝናቡ ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጸሚ የነበሩት ኢንጅነር አዜብ አስናቀ እና ሌሎች የዚህ ወንጀል ድርጊት ተሳታፊ ናቸው የተባሉ 50 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንደተመሰረተባቸው አቶ ዝናቡ ገልፀዋል።

ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር ስለመዋላቸው የተጠየቁት የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ህዝብ ግነኙነት አቶ ዝናቡ ቱኑ፤ "በእሱ ላይ ምላሽ መስጠት አልችልም" ብለዋል።

በኢንጂነር አዜብ እስናቀ የክስ መዝገብ የቀድሞ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኮለኔል ሙሉ ወ/ገብርኤል እንደሚገኙበት አቶ ዝናቡ ተናግረዋል።