ግብር አጭበርባሪዎች በማኅበራዊ ሚዲያ 'ፖስት' ሊታደኑ ነው

የስልክ ስክሪን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፈረንሳይ የዜጎቿን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በመፈተሽ ግብር አጭበርባሪዎችን ልትለይ ነው።

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በገጻቸው ላይ የሚለጥፉትን ፎቶግራፍና የግል መረጃ ዝርዝር (ፕሮፋይል) በማየት ግብር የከፈሉና ያልከፈሉ እንደሚለዩ ተገልጿል።

ድንጋጌው ባለፈው ሳምንት ከግብር ክፍያ ጋር በተያያዘ የወጣው ሕግ አካል ነው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የፈረንሳይ የመረጃ ደህንነት ክፍል ሕጉ እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል።

ሕጉን ያፀደቀው ምክር ቤት፤ እርምጃው የዜጎች ራስን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ጫና ሊያሳድር ቢችልም፤ ድንጋጌው የሚተገበርበት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ ብሏል።

ከቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱ በሚስጥራዊ ይለፍ ቃል (ፓስወርድ) የተቆለፉ ገጾችን ሰብሮ አለመግባት ሲሆን፤ የግብር ክፍያ ክፍሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለሕዝብ ይፋ የተደረጉ መረጃዎችን መጠቀም ግን ይችላል።

የፈረንሳይ መንግሥት የዜጎቹን የድረ ገጽ እንቅስቃሴ የሚቃኝበት የሦስት ዓመት እቅድ ነድፏል። ግብር ያልከፈሉ ሰዎችን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚለጥፉት መረጃ ማግኘት የዚሁ እቅድ አካል ነው።

የፈረንሳይ የመረጃ ደህንነት ክፍል የሦስት ዓመት እቅዱ ሕጋዊ አግባብነት ቢኖረውም፤ ግብርን በተመለከተ የወጣው ድንጋጌ የዜጎችን ነፃነት ይጋፋል ብሏል።

የበጀት ሚንስትሩ ጄራልድ ዳርማኒን በበኩላቸው "አጭበርባሪዎችን የምንገታበት አንድ መንገድ ነው" ሲሉ ሕጉን ገልጸውታል።

"በዚህ ዓመት ፈረንሳይ አልኖርኩም ብለሽ፤ ኢንስታግራም ላይ የፈረንሳይ ፎቶዎችን ብትለጥፊ ችግር አለ ማለት ነው" ሲሉ ለ 'ለ ፊጋሮ' ጋዜጣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።