በ2019 አፍሪካ ያጣቻቸው ታላላቆች

A selection of photos from those profiled Image copyright _

ሊገባደድ ጥቂት ቀናት በቀሩትየጎርጎሳውያኑ 2019 አፍሪካ ያጣቻቸውን ታላላቆች ቢቢሲ ዘክሯል።

ጥር

 • ኦሊቨር ምቱኩድዚ፣ ዚምባብዌ፣ ሙዚቀኛ፣ 66 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኦሊቨር ምቱኩድዚ

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1970ዎቹ የዚምባብዌን የነጭ ጨቋኝ አገዛዝ በመቃወም የአብዮቱ ድምፅ የሆነው ኦሊቨር ምቱኩድዚ የዚምባብዌ ምሰሶ ተደርጎ ይታያል። በቅፅል ስሙ "ቱኩ" የሚታወቀው ስመ ጥሩው ዘፋኝ ከፖለቲካው በተጨማሪ ኤችአይቪ ኤድስ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶችን በግጥሙ ውስጥ የሚያነሳ ሁለ ገብ አርቲስት ነበር።

 • ሁዋሪ ማናር፣ አልጀሪያዊ ሙዚቀኛ፣ 37
Image copyright Houari Manar/Facebook
አጭር የምስል መግለጫ ሁዋሪ ማናር

የአልጀሪያን የሃገረሰብ የባህል ሙዚቃ ወደፊት ማምጣት የቻለ፤ እንዲሁም አነጋጋሪ ጉዳዮችንም በሙዚቃው በመድፈሩም አልጀሪያውያን ያወሱታል። ህይወቱ ያለፈው የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና እያደረገ በነበረበት ወቅት ነው። ተችዎች በግጥሙ የሚያነሳቸው የማህበሩ ስስ ጉዳዮች መካከል የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መካተቱን ያወግዙታል።

 • አህመድ ሁሴን ሱዋሌ- ጋናዊ የምርምር ጋዜጠኛ፣ 31
አጭር የምስል መግለጫ አህመድ ሁሴን ሱዋሌ

በጋናዋ መዲና አክራ በሚገኘው የወላጆቹ ቤት በተተኮሰበት ጥይት የተገደለው ታይገር አይ (የነብር አይን) የሚል መጠሪያ ያለው የምርምር ጋዜጠኞች ቡድን አባል ነበር። በጋና በእግር ኳስ ሊጎች ላይ የተንሰራፋውን ሙስና ያጋለጠም የምርምር ዘገባም ሰርተዋል። ፖሊስ ከስራው ጋር በተያያዘ እንደተገደለ እምነት አለው።

የካቲት

 • ቢሲ ሲልቫ፣ ናይጀሪያዊ የጥበብ አሰናጅ (ኪውሬተር)፣ 56
Image copyright CCA, Lagos/Facebok
አጭር የምስል መግለጫ ቢሲ ሲልቫ

ኮንቴምፖራሪ ተብሎ በሚጠራው የአፍሪካ ጥበብ ትልቅ ስፍራ ያላት ቢሲ ሲልቫ በሌጎስ 'ኮንቴምፖራሪ አርት ኢን ሌጎስ' የሚባል ማዕከል እንዲሁም አሲኮ የተባለ ለመላው አፍሪካዊ ስነ ጥበብን የሚያስተምር የትምህርት ስርአት መስራች ናት። በመላው አለም የአፍሪካን ስነጥበብ ስራዎች የሚያንፀባርቁ አውደ ርዕዮችን አሰናድታለች። በጎርጎሳውያኑ 2014 ጄዲ ኦክሃይ ኦጄኬሬ የተባለው ፎቶግራፍ ስራዎችን የመሰነድን ጠቃሚነት አስመልክቶ ቢቢሲ ባናገራት ወቅት እየሞቱ ያሉ ባህሎችና ልምዶችን ልንጠብቃቸው ይገባል ብላለች።

 • ፍራንስ አልበርት ሬኔ- የሲቨልስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣ 83 አመት
Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ፍራንስ አልበርት ሬኔ

ሲሸልስ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ መውጣቷን ተከትሎ በጎርጎሳውያኑ 1977 በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ያዙ፤ ፍራንስ አልበርት ሬኔ ሲሸልስንም ለ27 አመታት ገዝተዋል።

ደጋፊዎቻቸው በሶሻሊስት ርእዮተ አለም የተቃኘ ልማት አምጥተዋል ቢሏቸውም ተችዎቻቸው ግን ጨቋኝ ነበሩ ይሏቸዋል።

 • ዶሮቲ ማሱካ፣ ዚምባብዌ-ደቡብ አፍሪካ የጃዝ ሙዚቀኛ፣ 83 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ዶሮቲ ማሱካ

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1950ዎቹ በደቡብ አፍሪካ ዝቅተኛው ማህበረሰብ ውስጥ በሙዚቃው አለም እንደ ጀግኒት የምትታይ ነበረች። የፖለቲካ ግጥሞቿም በአፓርታይድ አገዛዝ ዘንድ አልተወደደም፤ ብዙ ነገርም አስከፍሏታል። ዳንኤል ማላን ስለተባለው የአፓርታይድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የኮንጎ መሪ የነበሩት ፓትሪስ ሉምምባ አገዳደል ጋር የተያያዙ ሴራዎችን በግጥሟ ውስጥ ማካተቷም ለሰላሳ አመት ግዞት ዳርጓታል።

 • ካሮሊን ምዋታ፣ የኬንያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ 37 አመት
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ካሮሊን ምዋታ

ፖሊስ የሚያከናውናቸውን ግድያዎች አፈንፍኖ በመሰነድ የምትታወቀው ካሮሊን ምዋታ ለአምስት ቀናት ከጠፋች በኋላ አስከሬኗ በሌላ ሰው ስም ተመዝግቦ ተገኝቷል። ባለስልጣናቱም ህጋዊ ካልሆነ ፅንስ ማቋረጥ ጋር ሞቷን አያይዘውታል። አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቲ አምነስቲ ሞቷ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ ነው ብሎታል።

 • ቻርለስ ሙንጎሺ፣ ዚምባብዌ፣ ፀሃፊ፣ 71 አመት

አለም አቀፍ ዝናን ያተረፉት ስመ ጥር ፀሃፊ ቻርለስ ሙንጎሺ ታላላቅ ሽልማቶችን ማሸነፍ የቻሉ ናቸው። 'ካሚንግ ኦፍ ዘ ድራይ ሲዝን' የተሰኘው የአጫጭር ታሪኮች ስብብ የሆነው መፅሃፋቸው እንደ ጎርጎሳውያኑ 1972 ዚምባብዌን ያስተዳድር በነበረው ቅኝ ገዥም ታግዶ ነበር።

 • ክሪስ ካንታይ፣ ኬንያዊ ሂፕ ሆፕ ዘፋን፣ አርባ አመት
Image copyright ChrisKantadda/Facebook
አጭር የምስል መግለጫ ክሪስ ካንታይ

ካታንዳ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ራፐር በዘርፉ ፈር ቀዳጅ ከሆኑት ሙዚቀኞች አንዱ ነው። በግጥሞቹና በአዘፋፈኑም ስታይል በጎርጎሳውያኑ 2000ዎቹ መግነን ችሎ ነበር።

የካቲት

 • ሜድ ሆንዶ፣ ሞሪታንያ፣ ፊልም ዳይሬክተር፣ 82 አመት

የአፍሪካ ሲኒማ መስራች የሚባሉት ሜድ ሆንዶ በጎርጎሳውያኑ 1967 የሰሩት' ሶሌሊ' የሚል ርዕስ የተሰጠው ፊልምም በዘርፉ አድናቆትን ማትረፍ ችሏል። ታሪኩም አንድ ወጣት ስደተኛ በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ የሚያጋጥመውን ዘረኝነት የሚተርክ ነው። ኦኬይ አፍሪካ እንደዘገበውም ለኤዲ መርፊና ሞርጋን ፍሪማንን የመሳሰሉ ታላላቅ ተዋናዮችን ጨምሮ በሆሊውድ ለሚሰሩ ፊልሞች የፈረንሳይኛ ድምፆችን ወክለውም ሰርተዋል።

 • ኦክዊይ ኤንዌዞር፣ ናይጀሪያ፣ የጥበብ አሰናጅ (ኪውሬተር)፣ 55 አመት
Image copyright Manuel Toledo
አጭር የምስል መግለጫ ኦክዊይ ኤንዌዞር

ኦክዊይ ኤንዌዞር የአፍሪካ ጥበብ በአለም አቀፉ መድረክ ዘንድ እንደ ጥበብ በቁም ነገር ይወሰድ ዘንድ አስችሏል። በናጄሪያዋ ግዘት ካላባር የተወለደው ኦክዊይ ኤንዌዞር ትምህርቱን የተከታተለው በኒውዮርክ ነው። በኮንቴምፖራሪ የአፍሪካ ጥበብ ላይ የሚያጠነጥንም ኢንካ የተባለ መፅሄትንም የመሰረተው ከአስርታት አመት በፊት ነው። በ2015 የቬኒስ አውደ ርዕይን በ120 አመት ታሪክ ውስጥ በማሰናዳት (ኪውሬት በማድረግ) የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን ታሪክ ሰርቷል።

 • በርናርድ ዳዲዬ፣ አይቮሪኮስት፣ ፀሃፊ፣ 103 አመት
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በርናርድ ዳዲዬ

በምፀታዊ ስራዎቻቸው የሚታወቁት በርናንድ ዳዲዬ በቅኝ ግዛት ወቅት የነበረውን ዕውነታ በስራዎቻቸው ማሳዬት ችለዋል። 'ድራይ ዩር ቲርስ' (እንባችሁን ጥረጉ) የሚለውም ግጥማቸውም ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ የቻለ ስራ ሆኗል ።

 • ጋብርዬል ኦካራ፣ ናይጀሪያ፣ ደራሲ፣ 97 አመት

በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመፃፍ በአፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያው ከሆኑት አንዱ ጋብርዬል ኦካራ በተለይም በ1964 የፃፉት ዘ ቮይስ የሚለው ስራቸውም ብዙዎች አንብበውታል።

 • ሲማሮ ሉቱምባ፣ ኮንጎ፣ ሙዚቀኛ ፣ 81 አመት
Image copyright Ngoyarto
አጭር የምስል መግለጫ ሲማሮ ሉቱምባ

ለስስድስት አስርት አመታት ያህል የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሙዚቃ ዋልታና ማገር የነበሩት ሲማሮ የሙዚቃ ፀሃፊ፣ መሳሪያ ተጫዋች እንዲሁም አቀናባሪ ነበሩ። መሞታቸውም የዘመን ማብቂያ ነው ተብሎለታል።

 • ፒዬስ አደሳንሚ፣ ናይጀሪያ-ካናዳዊ ምሁር፣ 47 አመት
Image copyright CARLETON UNIVERSITY

በካናዳ የሚገኘው የካርልተን ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ጥናት ማእከል ዳይሬክተር የነበረው ምሁሩ ህይወቱ ያለፈው ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በተነሳ በደቂቃ ውስጥ አደጋ በደረሰበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።

ሚያዝያ

 • ሪቻርድ ሙዞኮ፣ ካሜሮንዶክተር፣ 42 አመት
Image copyright WHO/Twitter
አጭር የምስል መግለጫ ሪቻርድ ሙዞኮ

በዲሞከራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቡቴምቦ ግዛት የኢቦላ ህመምተኞችን እያከመ በነበረበት ወቅት በተተኮሰበት ጥይት ነው ዶክተር ሪቻርድ ሙዞኮ ህይወቱ ያለፈው።

 • አልፍሬድ ታባን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጋዜጠኛ፣ 62 አመት
አጭር የምስል መግለጫ አልፍሬድ ታባን

ካርቱም ሞኒተር የተባለው የመጀመሪያው ነፃ የእንግሊዝኛ ጋዜጠኛ መስራችና ዋና አዘጋጅ ነበር፤ ደቡብ ሱዳን ነፃነቷንም ማግኘቷንም ተከሎ ጋዜጣው ጁባ ሞኒተር የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ጋዜጠኛው አልፍሬድ ታባን በሙያውም ምክንያት በተደጋጋሚ ዘብጥያ የመውረድ ገፈት ቀማሽ ሆኗል።

 • ፓፒ ፋቲ፣ ብሩንዲ፣ እግር ኳስ ተጫዋች፣ 28 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ፓፒ ፋቲ

ለረዥም ጊዜ በልብ ህመም እየተሰቃዬ የነበረው ፓፒ ፋቲ በስዋዚላንዷ ከተማ እስዋቲኒ እየተካሄደ በነበረው ጨዋታ ራሱን ስቶ ከወደቀ በኋላ ህይወቱ አልፏል።

ግንቦት

 • ቢንያቫንጋ ዋይናይና፣ ኬንያ፣ ፀሃፊ፣ 48 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቢንያቫንጋ ዋይናይና

በአፍሪካ ስነ-ፅሁፍ ዘርፍ ከፍተኛ ስፍራ የነበረው ቢንያቫንጋ በቋንቋው ውበት፣ በጠንካራ አቋሙ፣ በድፍረቱና አፍሪካንና ህዝቦቿን ማእከል ባደረገ ፅሁፎቹ ይታወቃል።

ከነዚህም ፅሁፎቹ መካከል 'ዋን ደይ አይ ዊል ራይት አባውት ዚስ ፕሌስ'፣ 'ሃው ቱ ራይት አባውት አፍሪካ' ይገኙበታል።

የምዕራቡ አለም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ህዝቦች በላይ የሚኖሩባትን አህጉር በተለይም በፀሃፍያን ዘንድ የምትመሰልበትን መንገድ ሽሙጣዊ በሆነ መልኩ በፃፈበት "ሃው ቱ ራይት አባውት አፍሪካ (ስለ አፍሪካ እንዴት መፃፍ እንችላለን) በሚለው ፅሁፉ ቢንያቫንጋ ዋይናይና

"የመፅሃፋችሁን ሽፋን በየቀኑ የምናገኛቸውን አፍሪካውያንን ፎቶ ሳይሆን ኤኬ 47 ጠመንጃን የተሸከመ፤ የሽምቅ ውጊያ የተራቆቱ ጡቶች፤ የገጠጡ አጥንቶችን አድርጉ" በማለት ምዕራባውያን ስለ አፍሪካ ሲፅፉ በተደጋጋሚ የሚያወጧቸውን ፎቶዎች በማየት በነገር ሸንቆጥ አድርጓቸዋል።

በአርባ ስምንት አመቱ ህይወቱ ያለፈው ቢንያንጋ ተቃውሞን የማይሸሽ፤ ብቻውን መቆም የማይፈራ ግለሰብ ነበር። ፖለቲካውን በግል ህይወቱ እስከ መጨረሻው ድረስ የኖረ፤ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ወንጀል በሆነባት ኬንያ፣ ስለ ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት የፃፈ፤ እንዲሁም በተደጋጋሚ ድፍረት የተሞላባቸውን ንግግሮች ያደርግ የነበረ ነው።

 • ሬጂናልድ ሜንጊ፣ ታንዛንያ፣ የሚዲያ ባለቤት፣ 75 አመት
Image copyright IPP
አጭር የምስል መግለጫ ሬጂናልድ ሜንጊ

በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጦችና የቴሌቪዝን ባለቤት የነበሩት ሬጂናልድ ሜንጊ በፎርብስ ግምት መሰረት ወደ 560 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት አከማችተዋል።

ሰኔ

 • ሞሃመድ ሙርሲ፣ግብፅ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣ 67
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሞሃመድ ሙርሲ

የቀድሞው የግብጽ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሙርሲ ፍርድ ቤት ውስጥ በድንገት ተዝለፍልፈው ከወደቁ በኋላ መሞታቸው የተዘገበው በዚህ አመት ነው።

ሙርሲ እንደ አውሮፓዊያኑ በ2013 ነበር በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣናቸውን የተነጠቁት።

በግብጽ ታሪክ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ይሁንታን ያገኙ የመጀመርያው ርዕሰ ብሔር ነበሩ። ያም ሆኖ አገሪቱን መምራት የቻሉት ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር። የሕዝብ ተቃውሞን ተከትሎ በአልሲሲ የተመራ ወታደራዊ ኃይል ሥልጣናቸውን ነጥቋቸዋል።

 • ሰዓረ መኮንን፣ ኢትዮጵያ፣ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣ 65 አመት
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሰዓረ መኮንን

ሰኔ 15፣ 2011 ዓ. ም. የደረሰው ጥቃት፤ ከተሾሙ አንድ ዓመት ከጥቂት ቀናት ብቻ የሆናቸውን የአገሪቱን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን ሕይወት ቀጥፏል። ከሳቸው በተጨማሪ በጡረታ የተገለሉትና በወቅቱ በጄኔራል ሰዓረ ቤት የነበሩት ሜጄር ጄኔራል ገዛዒ ከጠባቂያቸው በተተኮሰ ጥይት መገደላቸውን የሚመለከታቸው አካላት አስታውቀዋል።

ጥቃቱ በደረሰባቸው ሰዓት አማራ ክልል የ"መፈንቅለ መንግሥት" ሙከራን ለማክሸፍ ሲሠሩ እንደነበርም ተገልጿል።

 • ዴቪድ ኮሌን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አርቲስት፣ 81 አመት
Image copyright Goodman Gallery
አጭር የምስል መግለጫ ዴቪድ ኮሌን

በጨቋኙ አፓርታይድ ግዛትም ሆነ ከዚያ በኋላ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን መድረክ ያመቻቹ አርቲስት ነበሩ። ፀሃፊ፣ ሰዓሊና መምህር የነበሩት ዴቪድ ኮሌን የጆሃንስበርግ ዝቅተኛ ህይወትንም በስራዎቻቸው አንፀባርቀዋል።

ሐምሌ

 • ቦብ ኮሊሞር፣ ኬንያ፣ የስራ ፈጣሪ፣ ባለሃብት፣ 61 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቦብ ኮሊሞር

በምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ውስጥ ስኬታማው ሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ ቦብ ኮሊሞር፤ ህይወታቸውም ያለፈው በካንሰር ምክንያት ነው።

ቦብ ካሊሞር የካሪብያኗ ጉያና ሃገር ተወላጅ ሲሆኑ በዜግነት ደግሞ እንግሊዛዊ ነበሩ።

ቦብ ኮሊሞር የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሲሆን፤ በቆይታቸውም በሞባይል ስልክ ክፍያን መፈጸምን ጨምሮ ድርጅቱ በአካባቢው ሃገሮች ውስጥ ያለውን የመሪነት ደረጃ ጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ አስችለውታል።

 • ኖምህሌ ኢንኮዬኔ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ተዋናይት
Image copyright TEDxPortElizabeth
አጭር የምስል መግለጫ ኖምህሌ ኢንኮዬኔ

በ1960ዎቹ ውስጥ አፓርታይድን በመቃወም ከታገሉት የጥበብ ባለሙያዎች አንዷ ስትሆን በኬፕ ፐርፎርሚንግ አርትስ ቲያትርም በመተወን የመጀመሪያዋ ጥቁር ናት።

 • ማንድላ ማሴኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አስትሮናት( ጠፈርተኛ)፣ 30 አመት
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ማንድላ ማሴኮ

ጠፈርተኛ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ማንድላ ማሴኮ በጠፈር ላይ በመውጣት የመጀመሪያው ጥቁር ሲሆን፤ ህይወቱ ያለፈው በሞተር ሳይክል አደጋ ነው።

 • ሆዳን ናላያህ ሶማሊያ፣ ጋዜጠኛ፣ 43 አመት
አጭር የምስል መግለጫ ሆዳን ናላያህ

አብዛኛዎቹ መገናኛ ብዙኃን ሶማሊያን የጦርነት ቀጠና፣ ድርቅ እና ረሃብ የማይለያት፣ የእርዛትና ጥማት ተመሳሌት፣ እንዲሁም የእርስ በርስ እልቂት ምሳሌ አድርገው ነው የሚስሏት። አንዲት ሴት ግን ይህን ለመቀልበስ ተነሳች።

ይህቺ ሴት ሆዳን ናላያህ ትባላለች። ትውለደ ሶማሊያዊ የሆነችው ሆዳን ከ6 ዓመቷ ጀምሮ ካናዳ ነው ያደገችው። ይሁን እንጂ ልቧ ሁሌም ሶማሊያ ነው ያለው።

የሶማሊያን ውበት፣ መልካም ገጽታና የሕዝቧን ትስስር ለተቀረው ዓለም ለማሳየት ቆርጣ የተነሳች ሴት በመሆኗ ከዓመት በፊት ከካናዳ ወደ ሶማሊያ ተመለሰች።

ዓላማ ያደረገችው በዓለም ላይ እንደ አሸዋ የተበተኑ ሕዝቦቿን በተለይም ውጭ አገር ያደጉ የሶማሊያ ወጣቶችን ማነቃቃትና አገራችን እንዲወዱ ማድረግ ነበር።

የሞተችውም በደቡባዊ ሶማሊያ በአንድ ሆቴል ላይ በደረሰ ጥቃት ነው።

 • ቤጂ ካይድ ኤሴቢሲ፣ የቱኒዝያ ፕሬዚዳንት፣ 92 አመት
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ቤጂ ካይድ ኤሴቢሲ

በአለም ትልቁ ፕሬዚዳንት በመሆን ቱኒዝያን ለዘመናት መርተዋል።

ነሐሴ

 • ካካማን( ዳርሲ ኢራኮዜ)፣ ብሩንዲ፣ የዩቲዩብ ኮከብ
Image copyright Facebook/Kacaman
አጭር የምስል መግለጫ ካካማን

ካካማን በሚል ስም የሚታወቀው የስድስት አመቱ ህፃን ዳርሲይ ኢራኮዜ በኢንተርኔትና በቲያትር ቤቶች በሚያቀርባቸው ኮሜዲ ሥራዎቹ የሚታወቅ ሲሆን፤ ህይወቱ ያለፈው በወባ በሽታ ነው።

ዳርሲይ ከታዋቂው ብሩንዲያዊው ኮሜዲያን ኪጊንጊ ጋር ባለፈው ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ተውኗል። ከጊኪንጊ ጋር በድጋሜ የኮሜዲ ሥራዎችን ለማቅረብም እቅድ ይዞ እንደነበር ተገልጿል።

 • ኡይኔኔ ምርዌትያና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ተማሪ፣ 19 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ኡይኔኔ ምርዌትያና

በወቅቱ የኬፕታውን ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረችው ኡይኔኔ ምርዌትያና እቃ ለመውሰድ ፖስታ ቤት አቅንታ በነረበት ወቅት የቀድሞ የፖስታ ቤት ሰራተኛ ደፍሮ በብረት ዘንግ ገድሏታል።

የተማሪዋ መሞት በኃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፤ ብሔራዊ የተቃውሞ ሰልፍም ተደርጓል።

ከዚህም በተጨማሪ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቀጣይዋ እኔ ነኝ በሚል ሃሽታግም በኃገሪቷ ውስጥ የተንሰራፋውን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አጋልጧል።

 • ጆን ደ ማቲው፣ ኬንዊ ሙዚቀኛ፣ 52
Image copyright Jowa Productions
አጭር የምስል መግለጫ ጆን ደ ማቲው

የኩኩዩ ሙዚቃ ንጉስ መጠሪያ ያገኘው ጆን ደ ማቲው የሞተው በመኪና አደጋ ነው።

 • ዲጄ አረፋት (ዲዲር ሁዎን) ሙዚቀኛ፣ አይቮሪኮስት፣ 33 አመት
Image copyright Getty Images

የ33 አመቱ ዲጄ አረፋት ወይም አንጂ ዲዲየር የሞተው በሞተር አደጋ ነው።

ፈረንሳይኛ በሚናገሩ ሃገራት ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈው ዲጄ አረፋት የአይቮሪኮስት የዳንስ ሙዚቃ ተብሎ በሚጠራው ኩፔ ዴካልም ንጉስ የሚል ስያሜም ማትረፍ ችሏል።

በዘናጭነቱ የሚታወቀው ሙዚቀኛው ፈጣን የሆነ የከበሮ ምት፣ ሂፕሆፕ ቅላፄ ባለው ዘፈኖቹ ብዙ አድናቂዎችን ማትረፍ ችሏል።

 • ዳውዳ ጃዋራ፣ ጋምቢያ፣የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣ 95 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ዳውዳ ጃዋራ

ጋምቢያን ለሶስት አስርርት አመታት አንቀጥቅጠው የገዙ መሪ ነበሩ።

መስከረም

 • ሮበርት ሙጋቤ፣ ዚምባብዌ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣ 95 አመት
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሮበርት ሙጋቤ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1924 የተወለዱት ሮበርት ሙጋቤ የእንጨት ሠሪ ልጅ ናቸው። የተማሩት በሮማን ካቶሊክ ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ነበር።

ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ፎርት ሀሬ ዩኒቨርስቲ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ከተማሩ በኋላ፤ ጋና ውስጥ መምህር ነበሩ።

በህመም ሳቢያ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሙጋቤ ዚምባብዌ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የመጀመሪያው መሪ ናቸው። ሙጋቤ አገራቸው ዴሞክራሲ የሰፈነባት እንደምትሆን ቃል ገብተው ነበር።

ያሉት ግን አልሆነም። ዚምባብዌ በግጭት የምትናጥ፣ በሙስና የተጨመላለቀች፣ ኢኮኖሚዋ የተናጋ አገር ሆነች።

 • ቼስተር ዊልያምስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ የራግቢ ተጫወች፣ 49 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቼስተር ዊልያምስ

ከሁለት አስርት አመታት በፊት ብቸኛው ጥቁር ራግቢ ተጫዋች ነበር።

 • ዛይን ኢል አባዳን ቢን አሊ፣ ቱኒዝያ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣83 አመት
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ዛይን ኢል አባዳን ቢን አሊ

ቱኒዚያን ለሁለት አስርታት በኃያል ክንዳቸው የገዟት ዛይን ኢል አባዳን ቢን አሊ በ83 ዓመታቸው ያረፉት በዚህ አመት ነው።

ቢን አሊ ህልፈታቸው የተሰማው በጥገኝነት ከኖሩባት ሳኡዲ አረቢያ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ቱኒዝያን ለ23 አመታት ያህል የገዙ ሲሆን መረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማምጣት ይወደሳሉ።

ነገር ግን ፖለቲካዊ ነፃነትን በማፈንና ሙስና በተንሰራፋ ስርአታቸውም በከፍተኛ ሁኔታ ይተቻሉ።

በጎርጎሳውያኑ 2011 የህዝቡን አመፅ ተከትሎም ከስልጣን ተገርስሰዋል።

ጥቅምት

 • አይዛክ ፕሮሚስ፣ ናይጀሪያ፣ እግርኳስ፣ 31 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አይዛክ ፕሮሚስ

የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ሱፐር ኤግልስ አምበል ነበር።

 • አንዲሌ ጉምቤ፣ ተዋናይ፣ 36 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አንዲሌ ጉምቤ

ሲምባን በቲያትር ቤቶች ለአስር አመታት ተጫውቷል።

 • በርናርድ ሙና፣ ጠበቃ፣ ካሜሮን፣ 79 አመት
Image copyright ICTR
አጭር የምስል መግለጫ በርናርድ ሙና

በሩዋንዳ በደረሰው ዘር ጭፍጨፋ የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ምክትል አቃቤ ነበሩ።

ህዳር

 • ቦጋለች ገብሬ፣ ኢትዮጵያ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ 59 አመት
Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቦጋለች ገብሬ

በልጅነታቸው በግርዛት ምክንያት ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸዋል። ሦስት ጊዜ ያህል ከተደረገባቸው የጠለፋ ሙከራ አምልጠዋል። ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ በእርሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በእህቶቻቸውም ላይ ደርሶ ሁለቱን እህቶቻቸውን በግርዛት ምክንያት በሞት አጥተዋል።

በእስራኤል አገር በሂብሪው ዩኒቨርሲቲ ሙሉ የትምህርት ዕድል አግኝተው 'ማይክሮ ባዮሎጂ' እና 'ፊዚዮሎጂ' አጥንተዋል። ከዚያም በአሜሪካ አገር በማሳቹሴትስ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲም በ'ኢፒዲሚዎሎጂ' ሦስተኛ ድግሪያቸውን አግኝተዋል።

በ1989 ዓ.ም ወደ አገራቸው በመመለስ በእርሳቸው ላይ ሲደርስ የነበረው በደል በሌሎች ላይ እንዳይደርስ ለመሞገት ከምባታ ጠንባሮ ዞን የተጀመረውን እና 'ከምባቲ ሜንቲ ጌዝማ' [ኬ ኤም ጂ] ወይንም የከምባታ ሴቶች ራስ አገዝ በመባል የሚታወቀውን አገር በቀል ድርጅት መስርተዋል።

ድርጅቱ በአካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ከግርዛት እንደታደገ ይነገራል። "ያልተገረዘች ሴት ባል አታገኝም" የሚለውን የአካባቢውን የቆየ ልማድ ታግሎ፤ የነበረውን የግርዛት ሽፋን 3 በመቶ እንዲወርድ ያደረገ ታላቅ ተግባር ማከናዎናቸውን ብዙዎች ይናገሩታል።

 • ፆላኒ ግዋላ፣ ጋዜጠኛ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ 44
Image copyright Xolani Gwala/Twitter
አጭር የምስል መግለጫ ፆላኒ ግዋላ

ጋዜጠኛው ከካንሰር ጋር የሚያደርገውን ትግል በመናገሩ ብዙዎች የሚያደንቁት ግለሰብ ነበር።

 • ኢማስ ኤልማን፣ ሶማሊያ፣ ካናዳ ሰብአዊ መብት ተሟጋች
Image copyright @AlmaasElman
አጭር የምስል መግለጫ ኢማስ ኤልማን

በሞቃዲሾ በበራሪ ጥይት የሞተችው ኢማስ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነበረች።