አሜሪካ በታሪኳ ከፍተኛ የጅምላ ግድያ የተፈጸመበት ዓመት አስመዘገበች

ከቴክሳሱ ጥቃት በኋላ Image copyright Getty Images

ሊገባደድ ጥቂት ቀናት ብቻ በቀሩት የፈረንጆቹ 2019 አሜሪኳ በታሪኳ እጅግ ከፍተኛ የሚባል የጅምላ ግድያ ማስተናገዷ ተገለጸ።

አሶሺየትድ ፕረስ፣ ዩኤስኤ ቱዴይ እና ኖርዝኢስተርን ዩኒቨርሲቲ በትብብር ባጠናቀሩት መረጃ መሰረት በዓመቱ 41 ክስተቶች የተመዘገቡ ሲሆን በጥቃቶቹም 211 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

አንድ ጥቃት የጀምላ ግድያ ነው ተብሎ የሚፈረጀው ከጥቃት ፈጻሚው በተጨማሪ አራት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች ሲገደሉ ነው።

የቴክሳሱ የጅምላ ተኳሽ ከሥራ ተሰናብቶ ነበር ተባለ

የአእምሮ ጤና ሰባኪው ፓስተር ራሱን አጠፋ

በአሜሪካ በሚጠናቀቀው ዓመት ለበርካቶች ሞት ምክንያት ከሆኑት የጅምላ ግድያዎች መካከል በወርሀ ግንቦት ቨርጂኒያ ቢች 12 ሰዎች የተገደሉበትና ነሀሴ ላይ ደግሞ በኤል ፓሶ 22 ሰዎች የሞቱበት የሚጠቀሱ ናቸው።

በመረጃው መሰረት በአርባ አንዱም ጥቃቶች 33 የጦር መሳሪያዎች አገልግሎት ላይ የዋሉ ሲሆን ካሊፎርኒያ 8 የጅምላ ግድያዎችን በማስተናገድ ከሁሉም ግዛቶች ከፍተኛውን ቁጥር አስመዝግባለች።

መረጃው ሲያጠናቅሩ የነበሩት ባለሙያዎች እንደገለጹት ከፈረንጆቹ 1970 በፊትም ሆነ በኋላ እንዲህ አይነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጅምላ ግድያ ቁጥር አልተመዘገበም። በሁለተኝነት የተቀመጠው ዓመት ደግሞ 2006 ሲሆን፤ በወቅቱ 38 ጥቃቶች ተመዝግበዋል።

ምንም እንኳን 2019 ከፍተኛውን የጅምላ ድግያ ክስተቶች ቢያስተናግድም በ2017 ለ224 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ ጥቃቶችም የማይዘነጉ ናቸው። በዚሁ ዓመት በላስ ቬጋ የሙዚቃ ድግስ በመታደም ላይ የነበሩ ሰዎች ተኩስ ተከፍቶባቸው 59 ሰዎች በቦታው ሞተዋል።

ታላቋ ፀሐፊ ቶኒ ሞሪሰን ስትታወስ

በአሜሪካ አሁንም ዜጎች የጦር መሳሪያ እንዳይዙ ሙሉ በሙሉ መከልከል የተሳናት ሲሆን ይህን ያክል ዜጎች በየዓመቱ ህይወታቸውን እያጡ መንግሥት ለምን ዝምታን መረጠ? የሚሉ በርካቶች ናቸው።

በነሀሴ ወር ኤል ፓሶ ላይ 22 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጠንከር ያለ ውይይት በጦር መሳሪያዎች ዙሪያ እንደሚደረግ ገልጸው ነበር።