ቻይና የሕክምና ባለሙያዎችን ከጥቃት የሚከላከል አዲስ ሕግ አወጣች

ዶክተሮች በቻይና Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አዲሱ ሕግ ዶክተሮችን በሕክምና ስፍራ ከሚደርስ ጥቃት ለመከላከል ያለመ ነው

ቻይና የሕክምና ባለሙያዎችን ከጥቃት የሚከላከል አዲስ ሕግ አወጣች። የሕጉ መውጣት የተሰማው አንድ ዶክተር በምትሰራበት ቤጂንግ ሆስፒታል በስለት ከተወጋች በኋላ ነው።

እንደ ሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘገባ ከሆነ ሕጉ የትኛውም ተቋምም ሆነ ግለሰብ የሕክምና ባለሙያዎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንዲሁም ክብራቸውን የሚነካ ማስፈራሪያ ዛቻ እንዳይደርስ ያግዳል።

ሕጉ ከመጪው ሰኔ ጀምሮ ስራ ላይ ይውላል ተብሏል።

"ዓላማችን ችግሮችን ፈተን ገንዘብ ማግኘት ነው " የጠብታ አምቡላንስ ባለቤት

የሙያውን ፈተና ለመጋፈጥ ከከተማ ርቆ የሄደው ሐኪም

እቴጌ፡ የጡት ካንሰርን በቀላሉ በስልክዎ መለየት እንደሚችሉ ያውቃሉ?

ያንግ ዌን በአንድ ግለሰብ ጥቃት በደረሰባት ዕለት በቤጂንግ ሲቪል አቪየሽን አጠቃላይ ሆስፒታል በድንገተኛ አደጋ ህክምና ክፍል በመስራት ላይ ነበረች።

የቻይና መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ግለሰቡ በድንገተኛ አደጋ ህክምና ክፍል ውስጥ የሚታከም ዘመድ ነበረው።

የብሔራዊ ጤና ኮሚሽን ኃላፊ የሆኑት ዛሆ ኒንግ "በዚህ አደጋ እጅጉን ተናደናል፤ ተቆጥተናል። በተለይ ደግሞ አዲሱ ሕግ ሊወጣ እየተነጋገርን በነበረበት ወቅት መሆኑ አሳዝኖናል" ብለዋል።

በአዲሱ ሕግ መሰረት " የሕክምና ተቋማት አካባቢ መረበሽ ወይንም የሕክምና ባለሙያዎችን ደህንነትና ክብር አደጋ ላይ መጣል አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጣል ያደርጋል። ቅጣቱም የገንዘብ ወይንም የእስር ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በሕገወት መልኩ የሕሙማንን የግል የሕክምና ታሪክ ይዞ የተገኘ፣ ያወጣ ይቀጣል ሲል ይደነግጋል። "

በቻይና ሆስፒታሎች አካባቢ የሕክምና ባለሙያዎች በሚደርስባቸው ጥቃት ምክንያት ሲሞቱ ወይንም ግጭት ሲገጥማቸው የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም።

በኢትዮጵያ ለካንሰር ተጋላጮች እነማን ናቸው?

በ2018 ብቻ ሁለት የህክምና ባለሙያዎች በደረሰባቸው ጥቃት ሲሞቱ 12 ግጭቶችም ተፈጥረው እንደነበር ሲጂቲኤን የተሰኘው የመገናኛ ብዙኀን ዘግቧል።

በቅርቡ የተሰራ ጥናት ይፋ እንዳደረገው በቻይና ከሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች 85 በመቶዎቹ በሥራ ቦታቸው ላይ ጥቃትን አስተናግደው ያውቃሉ ይላል።

"ሰዎችን ከበሽታ የሚከላከሉ ዶክተሮችን ማን ይከላከልላቸው" ሲል የሚጠይቀው ይህ ጥናት በበሽተኛና በሐኪሙ መካከል ያለ ደካማ ተግባቦት፣ በመገናኛ ብዙኀን የሚቀርቡ የተዛቡ ዘገባዎችና የሕክምና ወጪ መብዛት ለጥቃቱ ምክንያት ናቸው ተብለው ተለይተዋል።

ጥቃቶች ከመደጋገማቸው የተነሳ አንዳንድ ሆስፒታሎች ለሕክምና ባለሙያዎች ራስን የመከላከል ትምህርት እየሰጡ ይገኛሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ