ኪም ጆንግ ኡን ሰሜን ኮሪያ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ የደህንነት ፖሊሲ ያስፈልጋታል አሉ

ኪም ጆንግ አን ቅዳሜና እሁድ በተደረገው የፓርቲያቸው ማእከላዊ ስብሰባ ላይ Image copyright Reuters

የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆን ኡን የአገራቸውን ደህንነት እና ሉአላዊነት ለማረጋገጥ "በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አዎንታዊ" ፖሊሲ ያስፈልጋል ማለታቸው ተሰማ።

ኪም ጆንግ ኡን ይህን ንግግር ባልተጠበቀ ሁኔታ ያደረጉት እሁድ እለት በፒዮንግያንግ የፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ እንደሆነ ተዘግቧል።

ኪም "በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አዎንታዊ" የደህንነት ፖሊሲ ምን እንደሆነ ከማብራራት ግን ተቆጥበዋል።

ትራምፕ እና ኪም ተገናኙ

ሰሜን ኮሪያ 'ሮኬት ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ መሆኗን' የሚያሳይ ምስል ተገኘ

ኪም ጆንግ ኡን ሩስያ የመግባታቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል

ይህ የኪም ንግግር አገሪቱ የኒውክሌር መሳሪያ ማምረቷን በማቆም ረገድ ከአሜሪካ ጋር እያደረገች የነበረው ድርድር ማብቂያ ሊሆን ይችላል፤ ብሎም ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መሳሪያዎችን ወደ መሞከር ትገባለች የሚል ስጋትን በስፋት አጭሯል።

ይህ የኪም ጆንግ ኡን ንግግርን አሜሪካ "እጅግ አሳዛኝ" ብላዋለች።

ባለቀው የአውሮፓውያኑ 2019 መጀመሪያ ላይ የኒውክሌር ድርድራቸውን በሚመለከት ዓመቱ ማብቂያ ላይ አሜሪካ ትርጉም ያለው እርምጃ ካልወሰደች ሰሜን ኮሪያ "አዲስ አካሄድ" እንደምትከትል ፒዮንግያንግ አስጠንቅቃ ነበር።

ኪም እሁድ እለት ይህን ንግግር ማድረጋቸው ከመዘገቡ በፊት የዋይት ሃውስ የብሄራዊ የደህንነት አማካሪ የሆኑት ሮበርት ኦብሬን ለሰሜን ኮሪያ ምላሽ ለመስጠት አሜሪካ ብዙ አማራጭ አላት ማለታቸውን ኤ ቢ ሲ ዜና ዘግቧል።

"ኪም ጆንግ ኡን ያሉትን አማራጭ የሚወስዱ ከሆነ በጣም እናዝናለን፤ ይህንንም በተግባር እናሳያለን" ብለዋል።