ኢራን፤ የዩክሬን አውሮፕላን በሚሳኤል ሲመታ ቀርጿል ያለችውን ግለሰብ አሰረች

በአደጋው ለተጎዱት የመታሰቢያ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝደንት ሮሃኒ የአውሮፕላኑ አደጋ ይቅር የማይባል ስህተት ነው ብለዋል

ኢራን፤ የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን በሚሳኤል ሲመታ የሚያሳየውን ቪዲዮ ቀርጿል ያለችውን ግለሰብ ማሰሯን አስታወቀች።

በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ከብሔራዊ ደህንነት ጋር ተያይዞ ክስ ሊመሠረትበት ይችላልም ተብሏል።

የበረራ ቁጥሩ PS752 የመንገደኞች አውሮፕላን ከቴህራን አየር ማረፊያ ከተነሳ በኋላ ነበር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በሚሳኤል ተምትቶ የወደቀው። በዚህም ተሳፍረው የነበሩ 176 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ኢራን የተከሰከሰውን አውሮፕላን የመረጃ ሳንዱቅ ለአሜሪካ አልሰጥም አለች

'ትልቅ ስህተት ፈፅመሻል!' ዶናልድ ትራምፕ ለኢራን ያስተላለፉት መልዕክት

የአውሮፕላኑ አደጋ ምክንያት ሲያወዛግብ ቢቆይም፤ በኋላ ላይ ኢራን አውሮፕላኑ በስህተት መመታቱን ገልፃ ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን አስታውቃለች።

የኢራኑ ፕሬዚደንት ሀሰን ሮሃኒ የአደጋው ምርመራ በልዩ ፍርድ ቤት ይታያል ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው "ይህ እንደተለመደውና ሁል ጊዜ እንደሚያጋጥም ጉዳይ አይሆንም፤ መላው ዓለም የፍርድ ቤቱን ሂደት ይከታተላል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዚደንቱ አክለውም "በጣም አሳዛኝ የሆነው አጋጣሚ በአንድ ግለሰብ ብቻ ሊሳበብ አይገባም፤ ችግሩን የፈጠረው አንድ ሰው ብቻ አይደለም፤ ሌሎችም ተጠያቂዎች ናቸው" ብለዋል።

ምንም እንኳን ኢራን በመጀመሪያ አውሮፕላኑ በሚሳኤል መመታቱን ብትክድም፤ በኋላ ላይ ግን የመንገደኞቹ አውሮፕላን በአገሪቷ አየር መከላከያ መመታቱን አምናለች።

ይህንን የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስልም በማህበራዊ ሚዲያዎች ከተለቀቀ በኋላ፤ ተንታኞች ተንቀሳቃሽ ምስሉን በመመልከት አውሮፕላኑ በሚሳኤል ነው የተመታው ወደሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

የታሰረው ግለሰብ ማን ነው?

የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት አውሮፕላኑ በሚሳኤል ሲመታ የሚያሳየውን ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ያጋራውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር አውሎታል።

ይሁን እንጅ በመጀመሪያ ምስሉን ያጋራው እና የመረጃ ምንጩ አስተማማኝ መሆኑን የገለፀው፤ ተቀማጭነቱን በለንደን ያደረገው ኢራናዊ ጋዜጠኛ፤ የኢራን ባለሥልጣናት የተሳሳተ ሰው ማሰራቸውን ተናግሯል።

ማክሰኞ ዕለት የኢራኑ ሕግ አስፈፃሚ ቃል አቀባይ ጎላምሆሴን ኢስማኢሊ፤ ከአውሮፕላኑ ተመትቶ መውደቅ ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልፀዋል።

ቃል አቀባዩ ሕገ ወጥ በሆነ እና በቅርብ በተካሄደ የመንግሥት ተቃውሞ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ 30 ሰዎች መታሰራቸውንም አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ኒውዮርክ ታይምስ፤ በደህንነት ካሜራ የተቀረፁ ምስሎች እንደሚያሳዩት በ20 ሰከንዶች ልዩነት ሁለት ሚሳኤሎች በአውሮፕላኑ ላይ ሲተኮሱ ያሳያል ብሏል።

ይህ የአውሮፕላኑ መልዕክት ማስተላለፊያ [ራዲዮ መልዕክት መቀበያ] በሚሳኤል ከመመታቱ በፊት ለምን መሥራት እንዳቆመ ያሳያል። ብልሽት ያጋጠመው በመጀመሪያ በተተኮሰው ሚሳኤል ነበር ሲል ጋዜጣው አትቷል።

አደጋውን አስመልክቶ አገራት ምን ብለው ነበር?

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ፤ አውሮፕላኑ ከምድር ወደ ሰማይ ተወንጫፊ በሆነ ሚሳኤል ተመትቶ ስለመጣሉ ብዙ የደህንነት መረጃዎች ደርሰውኛል ብለው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ትሩዶ፤ ባገኙት መረጃ መሠረት ኢራን አውሮፕላኑን ሆነ ብላ አልመታችም።

"ካናዳውያን ጥያቄዎች አሏቸው። ለጥያቄዎቻቸውም ምላሽ ማግኘት ይገባቸዋል" በማለት በአደጋው ዙሪያ ዝርዝር ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ለአደጋው የትኛውንም አካል ተጠያቂ ለማድረግም ሆነ ሙሉ በሙሉ ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ጊዜው ገና መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወቃል።

ኢራን የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላንን በስህተት መትታ መጣሏን አመነች

በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍረው ከነበሩት 178 ሰዎች መካከል 63 ካናዳውያን ሲሆን፤ ከዩክሬኗ ኪዬቨ ወደ ቶሮንቶ ካናዳ የሚያቀኑ ነበሩ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ''ከዚህ አውሮፕላን ጋር በተገናኘ ጥርጣሬ አለኝ። የሆነ አካል ስህተት ሳይሰራ አይቀርም'' ከማለት ውጪ ዝርዝር ነገር መናገርን አልፈቀዱም ነበር።

የዩናይት ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንም፤ ሃገራቸው ከካናዳ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የዩክሬን የደህንነት ኃላፊ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ሦስት ምክንያቶችን አስቀምጠው ነበር። እነዚህም፦

  • አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ እንደ ድሮን ካሉ ሌላ በራሪ አካል ጋር ተጋጭቷል።
  • የሞተር ብልሽት ወይም በቴክኒክ ችግር ምክንያት አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ ጋይቷ ወይም ደግሞ
  • በሽብር ጥቃት ከአውሮፕላኑ ውስጥ ፍንዳታ አጋጥሟል የሚሉ መላ ምቶችን አስቀምጠው ነበር።

ኢራን ምን ብላ ነበር?

የኢራን ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኃላፊ አሊ አቤደዛዱህ "አውሮፕላኑ በምዕራብ አቅጣጫ ከአየር ማረፊያ ተነስቶ መብረር ከጀመረ በኋላ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ወደ ቀኝ ዞሮ ተመልሶ ለማረፍ እየመጣ ሳለ ነው የተከሰከሰው" ብለው ነበር።

ኃላፊው ጨምረውም የዓይን እማኞች አውሮፕላኑ አየር ላይ ሳለ በእሳት ተያይዞ ማየታቸውን ገልጸዋል።

"በሳይንሳዊ መንገድ ከተመለከትነው፤ ይህ አውሮፕላን በሚሳኤል ተመትቶ ነው የወደቀው የሚለው የሚያስኬድ አይደለም" ማለታቸውም ይታወሳል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ