የኢራኑ ፕሬዝደንት ስለ አውሮፕላኑ ተመቶ መውደቅ ጦሩ ማብራሪያ ይስጥ አሉ

የቴህራን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ምስል ይዘው። Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የቴህራን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ምስል ይዘው።

የኢራኑ ፕሬዝደንት ሃሰን ሩሃኒ እንዴት የመንገደኞች አውሮፕላን በስህተት ተመቶ ሊወድቅ እንደቻለ ጦሩ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አለበት አሉ።

ፕሬዝደንት ሩሃኒ "በመጀመሪያ የሚቀድመው ነገር፤ ሕዝቡን በትክክል ምን እንደተፈጠረ ማሳወቅ ነው። የሚወዷቸው ሰዎች በኛ ስህተት ሕይወታቸው ማለፉን ሲረዱ ሃዘናቸው ይበረታል" ብለዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ አህመድ ጃቫድ ዛሪፍ በበኩላቸው ኢራናውያን አደጋው ከተከሰተ በኋላ ለቀናት 'ተዋሽተው' ነበር ብለዋል።

ጃቫድ ዛሪፍ እንደሚሉት ከሆነ እሳቸውና ፕሬዝደንቱ ስለጉዳዩ ሳይነገራቸው ቆይተዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ጦሩ አውሮፕላኑ ተመቶ ለመውደቁ ኃላፊነት ላለመቀበል አለመዳዳቱ በራሱ የሚያስመሰግነው ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላንን በሚሳኤል መትቶ መጣሉ ለ176 ንጹሃን ዜጎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

በ30 ሰክንዶች ልዩነት የተስወነጨፉ ሁለት ሚሳዔሎች አውሮፕላኑን ስለመምታታቸው ተረጋግጧል። ከዚህ ቀደም የነበረው ግምት አውሮፕላኑ አንድ ግዜ ብቻ በሚሳኤል እንደተመታ ነበር።

የበረራ ቁጥር ፒኤስ751 በስህተት ተመቶ ከወደቀ በኋላ፤ የኢራን ባለስልጣናት አውሮፕላኑ በቴክኒክ ችግር ነው የተከሰከሰው ከማለታቸው በተጨማሪ መረጃዎችን ለመሰወር የአደጋውን ስፍራ በከባድ ማሽኖች ቁፋሮ ማካሄዳቸው፤ በኢራናውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማስማት አደባባይ በወጡ ኢራናውያን ላይ ጥይት ተኩሷል ተብሎ የቴህራን ከተማ ፖሊስ እጅጉን እየተብጠለጠለ ይገኛል።

ቀደም ሲል ካናዳ፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኢራቅ እና ዩክሬን አውሮፕላኑ በሚሳኤል ተመቶ ስለመውደቁ መረጃ አለን ቢሉም፤ ኢራን አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በቴክኒክ ችግር ነው ለማለት የቀደማት አልነበረም።

ብርጋዴር ጀነራል አሚር አሊ ሃጂዛዴህ የአብዮታዊ ጥበቃ አየር ክልል ኮማንደር እንደሚሉት ከሆነ፤ አንድ የሚሳኤል ኦፕሬተር ብቻውን/ብቻዋን ማንንም ሳያማክር/ሳታማክር እርምጃ ተወስዷል።

ትናንት የኢራን አቃቢ ሕግ ቃል አቀባይ፤ ለአውሮፕላኑ መመታት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን ተናግረዋል።

ኢራን፤ የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን በሚሳኤል ሲመታ የሚያሳየውን ቪዲዮ ቀርጿል ያለችውን ግለሰብም ስለማሰሯ ዛሬ ጠዋት ተሰምቷል።

በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ከብሔራዊ ደህንነት ጋር ተያይዞ ክስ ሊመሠረትበት ይችላልም ተብሏል።