ሴት በመምሰል ጋብቻ የፈፀመው ግለሰብ 'ከተፈጥሮ ጋር በሚቃረን ድርጊት' ተከሰሰ

ሀሰተኛው ሙሽራ

የፎቶው ባለመብት, The Daily Monitor

ሴት በመምሰል ከኢማሙ ጋር ጋብቻ የፈፀመው ግለሰብ 'ከተፈጥሮ ጋር በሚቃረን ድርጊቱ' ክስ እንደተመሠረተበት ዘ ዴይሊ ሞኒተር ጋዜጣ ዘገበ።

የግለሰቡ፣ ሪቻርድ ቱሙሻቤ እውነተኛ ማንነት የተገለጠው የጎረቤቱን ቴሌቪዥንና ልብሶች በመስረቅ ወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ነበር።

"ግለሰቡ ያለሁበት ሁኔታ ድርጊቱን እንድፈፅም አስገድዶኛል" ሲልም የኢማሙ ሀሰተኛ ሙሽራ ድርጊቱን ስለመፈፀሙ አምኗል።

ሼህ ሞሃመድ ሙቱምባ ሂጃብ ለባሿ 'ሚስታቸው'፣ ሰዋቡላህ ናቡኬራ ወንድ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ክፉኛ ነበር የደነገጡት።

ከአገሪቷ ዋና መዲና ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ክያምፒሲ በተባለች መንደር በሚገኝ መስጊድ ኢማም የሆኑት ሼህ ሙቱምባ፤ በነበሩት የጫጉላ ጊዜያት 'ከሙሽራቸው' ጋር ወሲባዊ ግንኙነት አልነበራቸውም።

ከሙሽራቸው ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ያልፈፀሙትም ሙሽሪት "የወር አበባ ላይ ነኝ" በማለቱ ነበር።

ቱሙሻቤ ባለፈው ማክሰኞ በማጂስትሬት ፍርድ ቤት ሲቀርብ ይቅርታ እንዲጠይቅ አልተጠየቀም። እስከ ቀጣዩ ቀጠሮ የፈረንጆቹ ጥር 24 ድረስ በቁጥጥር ሥር ውለው እንዲቆዩ ታዟል።

የፍርድ ቤቱ ዳኛ አለን አኬቶ፤ ለቱሙሻቤ የዋስትና መብት የመጠየቅ እድል እንዳላው እና ጉዳዩ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚላክ ነግረውታል።

በእምነት ተቋሙ ካላቸው ኃላፊነት የታገዱት ሼህ ሙቱምባ ግን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

የአካባቢው ካዲ [የእስልምና ዳኛ] ሼህ አብዱል ኑር ካካንዴ በበኩላቸው፤ አጋጣሚው ያልተጠበቀ መሆኑን ገልፀው በኢማሙ ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

ጋዜጣው ሼህ ሙቱምባ በሚያስተምሩበት መስጊድ ዋና ኢማም የሆኑትን ሼህ ኢሳ ቡሱልዋን ጠቅሶ እንደዘገበው የእስልምና ኃይማኖትን ላይ ያለውን እምነት ለመጠበቅ ሲባል ኢማሙ ከኃላፊነታቸው ታግደዋል።